ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን እየተሰራ ነው - ምክትል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ

87
መስከረም 29/2012 ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። የኦሮሚያ የግብርና ህብረት ስራ ማህበራት ፌዴሬሽን 42 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በገላን ከተማ የተገነባው የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመርቆ ስራ ጀምሯል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካ በቀን ከ1 ሺህ 200 በላይ ኩንታል የግብርና ምርቶችን ያቀነባብራል ተብሏል። በዚሁ ወቅት ምክትል ፕሬዝዳንቱ እንደተናገሩት፤ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው። ''አርሶ አደሩ የሚያመርታቸውን ምርቶች በማቀነባበር ከምርቱ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆን ፌዴሬሽኖችና የህብረት ስራ ማህበራት የበለጠ እንዲጠናከሩ የክልሉ መንግስት ድጋፍ ያደርጋል'' ብለዋል። በገጠር አካባቢዎች ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ በገጠር ተደራሽ እንዲሆን መንግስት ከባንኮች ጋር እየተነጋገር መሆኑንም ጠቁመዋል። የህብረት ስራ ማህበራት እንዲጠናከሩ መንግስት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን እያቀነባበር ለአገር ውስጥም ሆነ ለዓለም ዓቀፍ ገበያ እንዲያቀርብ ሁሉንም አርሶ አደር እንዲያሳትፍ መንግስት ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል። የክልሉ መንግስት የፌዴሬሽኑን የመሬት ጥያቄ ለመመለስ ቅድሚያ በመስጠት የሚመልስ መሆኑን ተናግረዋል። በክልሉ የኢኮኖሚ አብዮት ለማምጣት የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ድህነት ለመቀነስ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። ከሶስት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደር አባላት ያሉት ፌዴሬሽኑ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስከበረች በላይነህ እንዳሉት፤ ፋብሪካው አሁን በቀን 1 ሺህ 200 ኩንታል የሰብል ምርቶችን ያቀነባብራል። ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ደግሞ እስከ አምስት ሺህ ኩንታል የማቀነባበር አቅም የሚኖረው መሆኑን ጠቁመዋል። ፋብሪካው አርሶ አደሮችን በገበያ በማስተሳሰር የጎላ ጥቅም እንደሚሰጥ አመልክተዋል። ፋብሪካው በቆሎ የሚያመርቱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግና ከዚህ በፊት አምራቾች ያለባቸውን የገበያ ችግር የሚፈታና በማከማቻ ቦታ እጥረት ያጋጥም የነበረውን የምርት መበላሸት የሚያስቀር እንደሆነ ገልጸዋል። በፋብሪካው ምርቃት ላይ የተገኙት ዩኒዬኖችና አርሶ አደሮች በበኩላቸው የፋብሪካው መከፈት ከገበያ ትስስር ጋር ያለውን ችግር እንደሚቀርፍላቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። አቶ አሰፋ ለማና አቶ አህመዲህ ረሺድ እንደሚሉት፤ የማቀነባበሪያው ፋብሪካ መገንባት ምርቶች ላይ እሴት የመጨመርና የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ እንደሚያግዛቸው ጠቁመዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም