ወርኃዊ የትምህርት ተቋማት የጽዳት ዘመቻ ነገ ይጀምራል

167
መስከረም 29/2012 በየወሩ መጨረሻ አርብ በሁሉም የትምህርት ተቋማት የጽዳት ዘመቻ ተግባራዊ እንዲሆን በ29ኛው የትምህርት ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ዘመቻው እንደሚጀመር ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል። በጅግጅጋ የተካሄደው 29ኛው የትምህርት ጉባኤ ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ አንዱ የከተሞችና የትምህርት ተቋማት ውብና ማራኪ ማድረግ መሆኑ የሚታወስ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባስጀመሩት ወርሃዊ የጽዳት ዘመቻ መርሃግብር መነሻነት በትምህርት ተቋማት ወርሃዊ የጽዳት ዘመቻ ያካሂዳሉ። በመሆኑም ወርሃዊ የጽዳት ዘመቻው ከነገ የሚጀምር መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጽዮን ተክሉ ተናግረዋል። በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ላይ በተቀመጠው መሰረት የትምህርት ማህበረሰቡ በተለይም ተማሪዎች ስነ-ምግባር፣ ችግኝ እንክብካቤና ጽዳት የዕለት ተዕለት ስራቸውና ባህል እንዲያደርጉ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል። ተማሪዎች፣ መምህራንና ወላጆች ጨምሮ የትምህርት ማህበረሰቡ በአጠቃላይ የመማር-ማስተማር ሂደቱን ምቹና ተስማሚ እንዲሆን የድርሻቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል። የጽዳት ዘመቻውን የሚከታተል አሰራር ተዘርግቶከሚኒስቴሩ ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ግዴታቸውን እንዲወጡ የማሳወቅ ስራ መከናወኑን ገልጸዋል። መርሃ-ግብሩ በዳግማዊ ሚኒሊክ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተለያዩ አካላት በተገኙበት በይፋ እንደሚጀመር ታውቋል። ከጧቱ 1:30 ተጀምሮ 5:30 በሚጠናቀቀው ፕሮግራም ላይ የትምህርት ቤቱን ቅጥር ግቢ የማጽዳትና ችግኞችን የመንከባከብ ተግባር ይከናወናል። ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ሁሉንም ትምህርት ቤቶች “የአረንጓዴ ኢትዮጵያ ሞዴል” ለማድረግ በትምህርት ተቋማት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም እንደሚያካሂድ ገልጿል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም