የካናዳ ባለሃብቶች ቡድን በመጪው የካቲት በኢትዮጵያ የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት ያደርጋል

60
መስከረም 29/2012 የካናዳ ባለሃብቶች ቡድን በየካቲት ወር 2012  በኢትዮጵያ የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንደሚያደርግ ተገልጿል። የካናዳ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ኢትዮጵያ ጥሪ አቅርባለች። በካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከኩቤክ መንግስት የኢኮኖሚ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ጋር በትብብር ያዘጋጁት  የኢንቨስትመንት ፎረም ትናንት በካናዳ ሞንትሪያል ከተማ ተካሄዷል። የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የካናዳ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ አዋጭ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ የባለሃብቶችንና ታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ትኩረት መሳብ የቻለች አገር መሆኗን አምባሳደሯ ገልጸዋል። የእድገቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥና ሰፊ የስራ እድሎችን ለመፍጠር መንግስት የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በተለይም የቢዝነስ ክንውን አመቺነትት ለማሻሻል እና የውጭ ባለሀብቶችን የሚያጋጥሙ መዋቅራዊና ከኢንቨስትመንት ህገ-ደንብ ጋር ተያይዘው ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ ሴክተሮች ጭምር ክፍት እየተደረጉ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የካናዳ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለ ነዋያቸውን በማፍሰስ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ወሳኝ ምዕራፍ መፈጠሩን ነው አምባሳደር ናሲሴ የተናገሩት። በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ ከ30 በላይ በማዕድን፣ ኢነርጂ፣ በኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ፣ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ቱሪዝም እና በማማከር አገልግሎት ላይ የተሠማሩ የካናዳ ባለሃብቶች መገኘታቸው በመግለጫው ተመልክቷል። በፎረሙ ላይ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እድሎች የሚያሳይ ገለጻ፣ የማዕድን ሃብት እና የቱሪዝም መስህቦች የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ቀርበዋል። ባለሃብቶቹም በቀረበው ገለጻ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት እድሎች ለመሳተፍ ፍላጎት ማሳየታቸው የተገለጸ ሲሆን ተጨማሪ ጥናት ለማካሄድ የባለሃብቶች ቡድን በቀጣይ በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንደሚያደርግም በመግለጫው ተጠቅሷል። ኢትዮጵያና ካናዳ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1965 ሲሆን እ.አ.አ በ2018 የሁለቱ አገሮች የንግድ ልውውጥ መጠን 170 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም