አብዛኞቹ ጨው አቀነባባሪዎች አስገዳጅ የጥራት መስፈርት አላሟሉም

112
ኢዜአ መስከረም 29 / 2012 ዓ ም  በኢትዮጵያ በጨው ምርት ማቀነባበር ከተሰማሩ ድርጅቶች አብዛኞቹ አስገዳጅ የጥራት መስፈርት አሟልተው የሚሰሩ እንዳልሆኑ ተገለጸ። ይህ የተገለጸው በአዲስ አበባ በተካሄደ የጨው ምርት ጥራትን ለማሻሻል ባለመ የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ነው። ኢትዮጵያ ለ100 ዓመት የሚሆን የጨው ሃብት እንዳላትና 550 ጨው አምራቾች እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ። በውይይቱ ላይ ጽሁፍ ያቀረቡት የምግብና የተለያዩ ምርቶች የጥራት አማካሪ አቶ አቤል አንበርብር እንዳሉት በአገሪቷ ከሚገኙ 10 ጨው አቀነባባሪ ድርጅቶች የጥራት መስፈርት አሟልተው እንደሚሰሩ ማረጋገጫ ያላቸው ሁለት ብቻ ናቸው። ይህ ደግሞ ህገ ወጦችን ከትክክለኛው አቅራቢ ለይቶ ጥራት ያለው ምርት ለህብረተሰቡ ለማድረስ እቅፋት ሆኗል ነው ያሉት። በኢትዮጵያ ከሌሎች ምግቦች በተለየ የጨው ምርት አስገዳጅ ህግ የወጣለት ቢሆንም ህጉ በአግባቡ እንዲተገበር ተቆጣጣሪ አካላት ሚናቸውን እየተወጡ አለመሆኑን ገልጸዋል። የጥራት መስፈርት አሟልተው በማይሰሩ ድርጅቶች ላይ አስተማሪ እርምጃ ባለመወሰዱ መስፈርቱን አሟልተው የሚሰሩት ጥቂቶች እንዲሆኑም አድርጓል። አስገዳጅ ህጉ አለመተግበሩና ጨው ተመርቶ ለህብረተሰቡ በፍጆታነት እስኪጠቀመው ድርስ ያለው ሂደት መርዘምም ለችግሩ በምክንያትነት ተጠቅሷል። አቀነባባሪ ድርጅቶች የጥራት ደረጃውን አሟልተው እንዲሰሩ ቁጥጥር አለማድረግና የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ አለማሳደግም እንዲሁ። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአገሪቷ ከሚመረተው ጨው 89 በመቶ የሚሆነው በውስጡ አዮዲን እንደለው ቢነገርም በማከማቸት፣ በማጓጓዝና በማሸግ ሂደት ችግር የንጥረ ነገሩ ይዘት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል ነው የተባለው። የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሲስተር ሂሩት ገብረሚካኤል የጨው ምርት አቅርቦቱ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ገልጸዋል። በማሸግና በማጓጓዝ ሂደት የሚደረገው የቁጥጥር መላላትና እርምጃ አለመውሰድ ለህብረተሰቡ የሚደርሰው ምርት የጥራት ደረጃው ዝቅ እንዲል አድርጓል። ለአምራችና አቀነባባሪ ድርጅቶች ከ50 ኪሎ በታች ለግለሰብ ደግሞ ከሶሰት ኪሎ በላይ ማሸግ እንደማይቻል ህጉ ቢደነግግም አብዛኞቹ እየተገበሩት አይደለም ብለዋል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የባለድርሻ አካላት በቅንጅት አለመስራት እንደሆነ ነው የጠቆሙት። የውይይት መድረኩ የሚታዩትን ክፍተቶች ለይቶ መፍትሄ ለማበጀት መዘጋጀቱን በመግለጽ። በኢትዮጵያ 90 በመቶ ጨው የሚመረተው በአፋር ክልል ደቢና እና አፍዴራ ላይ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም