የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ ባቡር ፕሮጀክት የኃይል አቅርቦት የመንግስትን ትኩረት ይሻል

103
መስከረም 29/2012  የኃይል አቅርቦት መዘግየት የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ ባቡር መስመር አደጋ እንዲጋረጥበት አድርጓል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከአዋሽ በመነሳት የተለያዩ ከተሞችን አቋርጦ ሃራ ገበያ የሚገባው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ ባቡር ፕሮጀክት ግንባታ በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ነው የተጀመረው። የአውሮጳፓን የጥራት ደረጃ መሰረት በማድረግ ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት 390 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተሰራ ሲሆን ከአዋሽ እስከ ኮምቦልቻ 270 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመጀመሪያው ምዕራፍ 99 በመቶ ተጠናቋል። እንደ ፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አብዱልከሪም መሃመድ ገለፃ ቀሪው የፕሮጀክቱ አንድ በመቶ ከኃይል አቅርቦት ጋር የተያያዘ ነው። የመጀመሪያው ምዕራፍ የሙከራ ጊዜ በማከናወን አገልግሎት መስጠት የሚችልበት ደረጃ ላይ ቢሆንም የኃይል አቅርቦት ችግሩ ወደኋላ ጎትቶታል ነው ያሉት። በኃይል አቅርቦቱ መዘግየት ምክንያት የባቡር መስመሩን ለመዘርጋት ጥቅም ላይ የዋሉ ቁሳቁሶች ለስርቆት ተዳርገዋል፤ ከአገልግሎቱ ሊገኝ የሚችለውም ጥቅም እየቀረ መሆኑን በአፅንኦት ገልጸዋል። እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ ፕሮጀክቱ ሲጀመር በኃይል አቅርቦት ጉዳይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ውይይቶች ሲደረጉ የነበረ ቢሆንም አቅርቦቱን በወቅቱ ማግኘት አልተቻለም። ኢንጂነር አብዱልከሪም አሁንም ባቡሩን ወደ አገልግሎት በማስገባት በመስመሩ ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመታደግ የኃይል አቅርቦት ችግሩ እንዲፈታ ጠይቀዋል። ግንባታውን የሚያከናውነው የቱርኩ "ያፒ መርከዜ" የግንባታ ተቋራጭ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ  ኢንጂነር እርሃን ሴንጅዝ በበኩላቸው ስራ ተቋራጩ በገባው ውል መሰረት የመጀመሪያ ምዕራፍ የግንባታ ስራዎችን በማጠናቀቁ ኃይል ካገኘ አገልግሎት ለማስጀመር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የኃይል ጣቢያዎችን ከባቡር መስመሮች የሚያገናኙ መስመሮች አለመዘርጋት ኃይል በወቅቱ እንዳይቀርብ አድርጎታል ብለዋል። መስመሮቹን ለመዘርጋት የሚያስፈልገው ገንዘብ አለመገኘት ለኃይል አቅርቦቱ መዘግየት ፈተና እንደሆነም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሁን ባለበት ከፍተኛ የብድር ጫና ተበድሮ ኃይል ሊያቀርብ የማይችል መሆኑን በመግለጽ መንግስት አማራጭ እንዲወስድ ለገንዘብ ሚኒስቴር ማሳወቁን ጠቁመዋል። መንግስት ከፍተኛ ወጪ የወጣበትን የባቡር መስመር ወደ ስራ ለማስገባት የገንዘብ አማራጮች ላይ ሊያተኩር እንደሚገባም አንስተዋል። የገንዘብ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሳ ደግሞ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር አለመኖሩን በስልክ ተናግረዋል። የፕሮጀክቱ ሁለተኛው ምዕራፍ 73 በመቶ የደረሰ ሲሆን አጠቃላይ የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልድያ/ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት አፈጻጸም 90 በመቶ መድረሱ ተገልጿል። የኃይል አቅርቦት ችግር ከተፈታ በተያዘው በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ በ2013 በጀት ዓመት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተነግሯል። ይህ የባቡር መስመር በአፋር ክልል ከምትገኘው አዋሽ ሰባት ተነስቶ በአዋሽ አርባና በአማራ ክልል ኮምቦልቻ፣ ሐይቅና መርሳ እንዲሁም ሌሎች ከተሞችን አቋርጦ እስከ ወልድያ/ሃራ ገበያ ይዘልቃል። በ1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚገነባው የባቡር መስመር ዝርጋታ ሲጠናቀቅም በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ያለውን የንግድ እንቅስቃሴና የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያሳልጥ ታምኖበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም