ዩኒዬኑ ከ200ሺህ በላይ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ማሰራጨቱን ገለጸ

65
ጎንደር መስከረም 29 / 2012  በጎንደር ከተማ የሚገኘው ጸሃይ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒዬን ያቋቋመው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከ200ሺህ በላይ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በማሰራጨት ገበያ አረጋግቼያለሁ አለ፡፡ ፋብሪካው አገሪቱ በዓመት ለፓልም ዘይት ግዢ የምታወጣውን 3ነጥብ 6ሚሊዮን ዶላር የማስቀረት አቅም አለው ተብሏል፡፡ የዩኒዬኑ ተወካይ አቶ ደረበ አቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዩኒዬኑ ፋብሪካውን ገበያውን ያረጋጋው የኑግ፣ የሱፍ ሌሎች የቅባት እህልን ተጠቅሞ ባመረተው ዘይት ነው። ዘይቱ በሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራትና  ዩኒዬኑ ባቋቋማቸው መሠረታዊ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማህበራት መሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡ ዩኒዬኑ ነጋዴዎች በሊትር 104 ብር የሚሸጡትን ዘይት በ85 ብር ሂሳብ በመሸጥ ዋጋ በማረጋጋት ሸማቹ የገበያ አማራጭ እንዲኖረው ከማድረጉም ባሻገር፣ ለ70 ወገኖችም ቋሚና ጊዜያዊ ሥራ መፍጠሩን አመልክተዋል። ፋብሪካው በዚህ ዓመት በሙሉ አቅሙ ወደ ማምረት በማሸጋገር በቀን 10ሺህ ሊትር ዘይት ለማምረት ግብዓቶች እያሟላ መሆኑን  ተወካዩ አመልክተዋል። በዚህም በዓመት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በማምረት ከውጭ የሚገባውን የፓልም ዘይት በመተካት የውጭ ምንዛሪ ለማዳን ያስችላል ብለዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ፋብሪካው በግብዓትነት የሚጠቀምበትን 10ሺህ ኩንታል ኑግና ሱፍ ከአርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ  በመረከብ ለአርሶ አደሮች የገበያ ትስስር መፍጠሩንም አቶ ደረበ አስታውሰዋል፡፡ የጎንደር ከተማ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የሸማቾች ቡድን መሪ ተወካይ አቶ እያዩ በላይ በከተማው መንግስት በድጎማ ከውጭ የሚያስገባው 668ሺህ ሊትር የፓልም ዘይት በየወሩ ለነዋሪዎች እንደሚያሰራጭ ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው መንግሰት ለዘይት ግዢ የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረቱም  በላይ፣ በምርቱ ላይ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው በምርት ጥራትም ሆነ በዋጋ የከተማው ነጋዴዎች ከሚያቀርቡት የተሻለ ነው ያሉት የጎንደር ከተማ ነዋሪዋዋ ወይዘሮ ባንቺ አላምረው ናቸው፡፡ ወይዘሮ ከበቡሽ ነጋ የየተባሉ ነዋሪ ፋብሪካው በከተማው ዘይት በተመጣጠነ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ አድርጎኛል ብለዋል። ዩንየኑ በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባቀፈው መሠረታዊ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማህበር አባል አርሶአደር መልኬ አያሌው አምና ያመረቱትን አራት ኩንታል በ14ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ዩኒዬኑ ፋብሪካውን ያስገነባው በ100 ሚሊዮን ብር ወጪ ነው። በ143 መሠሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት የተደራጁ 128ሺ የሚጠጉ አባላት አሉት።የየቋሚና ተንቀሳቃሽ ካፒታሉ መጠንም 110 ሚሊዮን ብር ደርሷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም