በደቡብ ወሎ ዞን በስንዴ ማሳ ላይ የተከሰተውን የቢጫ ዋግ በሽታ ለመከላከል እየተሰራ ነው

93
መስከረም 29/2012 በደቡብ ወሎ ዞን በሁለት ሺህ አንድ መቶ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በለማ የስንዴ ሰብል ላይ የተከሰተዉን የቢጫ ዋግ በሽታ ኬሚካል በመርጫት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያዉ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ይመር ሰይድ ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ የመኸር ወቅት ከ146 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ሰብል ለምቷል። ይሁን እንጂ ከመስከርም ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በ7 ወረዳዎች በሁለት ሺህ 100 ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም በተዘራ የስንዴ ሰብል ላይ የተከሰተዉ የቢጫ ዋግ በሽታ በምርታማነት ላይ ተጽኖ እንዳያሳድር የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው። እስካሁንም 415 ሊትር በመጠቀም 836 ሄክታሩን ከበሽታው መከላከል መቻሉን ጠቅሰው፤ ቀሪዉን በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ስር ለማዋል 600 ሊትር ኬሚኪል ከክልል ቀርቦ በየወረዳዉ መሰራጨቱን ገልፀዋል። በስንዴ ላይ የሚከሰተዉ የቢጫ ዋግ በሽታ በፈንገስ የሚመጣ መሆኑን የተናገሩት አቶ ይመር ገና ሲጀምር በኬሚካል መከላከል ካልተቻለ በደቂቃዎች ተስፋፍቶ ሙሉ በሙሉ ከምርት ዉጭ ያደርጋል ብለዋል፡፡ በመኸር ከለማው  አጠቃላይ መሬትም 30 በመቶ የስንዴ ሰብል እንደሚሸፍን ጠቁመዉ፤ ከለማው መሬትም ከአራት  ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል። በጃማ ወረዳ የ014 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር የሱፍ አብደላ በሰጡት አስተያየት በአንድ ሄክታር ማሳ ላይ በዘሩት ስንዴ የቢጫ ዋግ በሽታ ከሳምንት በፊት በመከሰቱ ለመከላከል ከግብርና ባለሙያዎች ጋር እየሰሩ ነዉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በየጊዜዉ በማሰስና ከተባይ በመከላከል ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ''በግማሽ ሄክታር ባለሙት የስንዴ ሰብል ላይ የተከሰተውን የቢጫ ዋግ በሽታ ኬሚካል በመርጨት እየተከላከልኩ ነው'' ያሉት ደግሞ አርሶ አደር ሰይድ ሙሄ ናቸው ። ''ለወደፊቱ ከስጋት ነጻ እንድንሆን በሽታዉን መቀቋቋም የሚችል ዝርያ በጥናት ተረጋግጦ ሊቀርብልን ይገባል'' ሲሉም አሳስበዋል። በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ ሰብሎች በመኸር ከለማዉ 441 ሺህ ሄክታር መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም