ዋግ ልማት ማህበር ለሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ተማሪዎች የመማሪያ ኮፒውተር ድጋፍ አደረገ

66
መስከረም 29 /2012 ዓ.ም የዋግ ልማት ማህበር /ዋልማ/ ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ 20 የመማሪያ ኮምፒውተሮችን ትናንት ለሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ድጋፍ አደረገ ፡፡ የልማት ማህበሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ በአምላኩ አበበ በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ድጋፉ በቴክኖሎጂ በመታገዝ የተሻለ እውቀት ያላቸው ተማሪዎችን ለማፍራት ያለመ ነው። ኮሌጁ የፈጠራ ክህሎታቸውን በማዳበር ቴክኖሎጂን የሚያፈልቁ ተማሪዎችን ለማፍራት የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ የልማት ማህበሩ ያደረገው የኮምፒዩተር ድጋፍ ከ400 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው መሆኑን ተናግረዋል ። ልማት ማህበሩ የብሄረሰብ አስተዳደሩን የትምህርት እንቅስቃሴ በልዩ ትኩረት እየደገፈ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰው በቀጣይነትም በሁለንተናዊ መንገድ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የሰቆጣ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኮሌጁ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ በሃይሉ መኮነን በበኩላቸው በልማት ማህበሩ የተደረገው የኮፒውተር ድጋፍ  የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያግዝ ነው ብለዋል ፡፡ በተለይም ተማሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር ያላቸውን ቁርኝት ከማሳደግ ባለፈ ተወዳዳሪና ጊዜው በሚጠይቀው ልክ የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት የኮሌጁን አቅም የሚያጎለብት መሆኑን ገልፀዋል። የሰለጠነና በቴክኖሎጅ የበለፀገ የሰው ሃይል ለማፍራት ልማት ማህበሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ምክትል ከንቲባው በቀጣይም ኮሌጁ ያሉበትን የግብዓት እጥረቶች ለመቅረፍ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በሰቆጣ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሀር ክብሩ ይስፋ መሰለ እንዳሉት ደግሞ ኮሌጁ ባሉት የኮምፒዩተር እጥረት ምክንያት ለተማሪዎች የተግባር ትምህርት ለመስጠት ሲቸገር መቆየቱን አስታውሰዋል። ባለፈው የትምህርት ዘመን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፍ ብቻ 205 ተማሪዎችን 18 በማይበልጡ ኮፒውተሮች ብቻ የተግባር ትምህርት ለመስጠት መገደዱን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የዋግ ልማት ማህበር ያደረገው ድጋፍ በዘርፉ ያጋጥም የነበረውን ችግር እንደሚቃልልላቸው ገልፀዋል። የሰቆጣ ቴክኒክና ሙያ ተቋም ከሃምሌ 1ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ማደጉ የሚታወስ ነው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም