ከ42 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባው የገላን የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመረቀ

64
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 29/2012 ከ42 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ በገላን ከተማ የተገነባው የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመረቀ። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካው በቀን ከ1 ሺህ 200 በላይ ኩንታል የግብርና ምርቶችን ያቀነባብራል ተብሏል። ፋብሪካው ባለቤትነቱ የኦሮሚያ ግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፌደሬሽን ሲሆን ለግንባታው ከ42 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ እንደተደረገበት ተጠቅሷል። የፌደሬሽኑ ዳይሬክተር ወይዘሮ አስከበረች በላይነህ እንዳሉት ፋብሪካው አሁን በቀን 1 ሺህ 200 ኩንታል የሰብል ምርቶችን የሚያቀነባብር ሲሆን በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር ደግሞ እስከ አምስት ሺህ ኩንታል የማቀነባበር አቅም እንደሚኖረው ተናግረዋል። ፌደሬሽኑ ከሶስት ሚሊየን በላይ አርሶ አደር አባላት እንዳሉት የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ ፋብሪካው አርሶ አደሮችን በገበያ በማስተሳሰር የጎላ ጥቅም እንደሚሰጥ አመልክተዋል። በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ 14 ዞኖችም ለፋብሪካው ግብዓት የሚሆን በቆሎ አምራች መሆናቸው ተገልጿል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም