የእንግሊዙ የደህንነት ተቋም በአፍሪካ ቀንድ እያደገ የመጣውን ሽብርተኝነት ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በቅንጅት ለመከላከል እንደሚሰራ ተገለጸ

72
መስከረም 28/2012 የእንግሊዙ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ በአፍሪካ ቀንድ እያደገ የመጣውን ሽብርተኝነት ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በቅንጅት ለመከላከል ከስምምነት ላይ መድረሱ ተጠቆመ። የእንግሊዙ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ በአፍሪካ ቀንድ እያደገ የመጣውን ሽብርተኝነት ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በቅንጅት ለመከላከል መስማማቱን ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል ከእንግሊዙ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ኃላፊ ሰር አሌክስ ያንገር ጋር በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ባለው ወቅታዊ የፀጥታና የሽብርተኝነት ስጋት ዙሪያ ዛሬ መክሯል። ኮሚሽነር ደመላሽ በዚሁ ጊዜ በአፍሪካ ቀንድ የሽብር እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉትን የአልሸባብንና የአይ ኤስ የሽብር ቡድኖች እንቅስቃሴን ለመግታት ሁለቱ ሀገራት የጀመሩትን የመረጃ ልውውጥ አጠናክረው በመቀጠል በአፍሪካ ቀንድ የሚስተዋለውን የሽብርተኝነት አደጋ ለመከላከል በጋራ እንደሚሰሩ መግባባት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል። ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት በሰው ኃይል፣ በአደረጃጀት፣ በአሰራርና በቴክኖሎጂ ራሱን ለማጠናከር የሚያስችሉ የሪፎርም ስራዎችን እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነር ደመላሽ፤ ተቋሙ ተልእኮውን በተሻለ መንገድ ለመፈፀም የሚያስቸለውን አመቺ የሆኑ የህግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ለኃላፊው ማብራሪያ መስጠታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል። የእንግሊዙ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስም በመረጃና ደህንነት ዘርፍ ያለውን የዳበረ ልምድ ለኢትዮጵያው አቻ ተቋም ለማካፈል ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑን በመግለጽ፤ ይህ ሁለቱም በአካባቢው ያለውን የሽብር አደጋና አለመረጋጋት በጋራ ለመከላከል ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። የሁለቱ  አገራት የመረጃና ደህንነት ተቋማት የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው የጠቀሱት ኮሚሽነሩ ይህን የቆየ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ መግባባት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል። የእንግሊዙ ሴክሬት ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ኃላፊ ሰር አሌክስ ያንገር በበኩላቸው በሁለቱ አገራት የፀጥታና የደህንነት የጋራ ጉዳዮች ዙሪያ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ዙሪያ ከዳይሬክተር ጀነራሉ ጋር ውይይት መደረጉን ገልፀው፤ በቀጣይ የፀረ-ሽብር እንቅስቃሴን በተመለከተ ስለሚኖራቸው የጋራ ትብብር መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል። በቅርቡ ኢትዮጵያ በሽብርተኞች ላይ የወሰደቻቸውን እርምጃ አድንቀው፤ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት እያካሄደ ያለው ሪፎርም ትልቅ የለውጥ እርምጃ በመሆኑ በቀጣይ ተቋማቸው ለአገልግሎቱ የአቅም ግንባታና የተሞክሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ መግለጻቸውን መግለጫው አትቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም