የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራሁ ነው፡- የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር

67
አዳማ ሰኔ 9/2010 አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ ማላመድና አጠቃቀም ዙሪያ መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ በዘርፉ የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሚናን ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን የግብርና እና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር ገለጸ። በዚሁ ስራ  በዘርፉ የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሚናን ማጠናከር በሚቻልበት ሂደት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እያሱ አብረሃ በዚህ ወቅት " አዲስ የተከለሰው የግብርና ልማት ፓኬጅን በተቀናጀ መልኩ ለመተግበርና አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ ማላመድና አጠቃቀም ዙሪያ መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጣ  በዘርፉ የተሰማሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ሚናን ማጠናከር ያስፈልጋል" ብለዋል። የመድረኩ ዓላማ በ2010/11 የምርት ዘመን የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳካትና 380 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ዘርፉን በቅንጅትና በተደራጀ መልኩ በቴክኖሎጂና አዳዲስ አሰራር ለመደገፍ   ያለመ መሆኑን ገልጸዋል። የግብርና ምርቱ ከምግብ ፍጆታነት ባለፈ በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉ የአግሮፕሮሰሲንግ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ፍላጎትን በዘላቂነት እንዲመግብ፣በቂ የውጪ ምንዛሪ ምንጭ እንዲሆንና ከውጪ የሚገባውን የግብርና ጥሬ እቃዎችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንዲቻል ተሳትፎቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ጭምር ነው። ዘርፉን ለማዘመን የባለድርሻ አካላትን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኘውን አመራርና ፈጻሚውን አካል በእውቀትና በክህሎት በማብቃትና አቅሙን መገንባት በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን ዶክተር እያሱ ተናግረዋል። በዚህ ላይ  27 በመቶ ላይ የሚገኘውን የሞዴል አርሶ አደሮች ድርሻ ከ50 በመቶ በላይ ለማድረስና በመጠን ላይ ብቻ የተወሰነው የግብርና እድገት ወደ መዋቅራዊ እድገት ለመለወጥ የተሟላ ፓኬጅ መተግበር  አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል። ተጠያቂነት ያለው ክትትልና ድጋፍ የመዘርጋት፣አርሶ አደሩ ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በወቅቱ እንዲያገኝ ማስቻል፣የግብርና ሠርቶ ማሳያ ማዕከላትን በሰው ሃይልና በቴክኖሎጂ  ድጋፍ የማብቃት ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝም ተመልክቷል። አርሶ አደሩ ከአዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጅ ጋር ማቆራኘት ለግብርና ምርትና ምርታማነት እድግት ወሳኝ  መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሰልፍ ሄልፕ አፍሪካ  የኢትዮዽያ ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ብረሃኑ ናቸው። ድርጅታቸው የድንች፣አፕል፣የቢራ ገብስና የተለያዩ የስንዴ ዝሪያዎችን ከግብርና ምርምር ማዕከላት ጋር በመሆን ለአርሲ፣ደቡብ ጎንደርና ለሰሜን ሸዋ አርሶ አደሮች ተደራሽ እያደረገ መሆኑንም  ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ገበያ ተኮር ሰብል እንዲያመርት አዲሱ የግብርና ስትራቴጂ ውጤታማ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው በቴክኖሎጂ ሽግግርና ቴክኒካዊ ድጋፍ  የሠርቶ ማሳያ ማዕከላትን ከማጠናከር ባለፈ ለፈጻሚዎች የክህሎትና የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡ በሳሳካዋ ግሎባል አፍሪካ የገበያ ትስስር ቡድን መሪ አቶ በሬቻ ቱሪ በበኩላቸው በቅድመ ምርትና ድህረ ምርት እንዴት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ "በተለይም በእርሻ ወቅት የግብዓትና ቴክኖሎጂ ጠቃቀም፣በአጨዳ፣ውቂያና ክምችት ወቅት የአነስተኛ መካናይዜሽንና ዘመናዊ የምርት ማከማቻዎችን  ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅ ረገድ በ253 የሠርቶ ማሳያ ማዕከላት እየሰራን እንገኛለን "ብለዋል። በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው  የምክክር  መድረክ  በግብርና ዘርፍ የሚሰሩ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም