ቢሮው በ42 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የልህቀት ማዕከል አስመረቀ

90
ድሬዳዋ ኢዜአ መስከረም 28 / 2012 የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በ42 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የልህቀት ማዕከል  አስመረቀ፡፡ የማዕከሉ መገንባት በየዘርፉ ጥናትና ምርምር በማድረግ በድሬዳዋ የተሻለ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንደሚያግዝ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡ የልህቀት ማዕከሉ ለቤተ-ሙከራና ጂምናዚየም፣ ካፍቴሪያ፣ ለጥናትና ምርምር፣ ለቤተ-መፅሐፍትና ለሌሎች በርካታ ጉዳዮች የሚያገለግሎ ዘርፎችን አካቷል፡፡ ማዕከሉን የመረቁት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር፣ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድና የአስተዳደሩ የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ናቸው፡፡ በምርቃቱ ላይ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ እንደተናገሩት፤ ከ42 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ይኸው ማዕከል በሁሉም መስክ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ‹ኮምፒውተራይዝ› ይሆናል፤ ቤተ-መፅሐፍቱ የጥናትና የምርምር ዘርፎቹም ‹ዲጂታላይዝድ› ይደረጋል፡፡ ማዕከሉ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጥና በዘመናዊ ዲጂታል ቁስ እንዲታገዝ በአውስትራሊያ የሚኖሩ የድሬዳዋ ተወላጆችና አንድ ፕሮፌሰር ማዕከሉን ጎብኝተው ቁሱን ለማሟላት ቃል መግባታቸውን ነው ወይዘሮ ሙሉካ የገለፁት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ትምህርት ቢሮ በዘንድሮ በጀት ዓመት ለማእከሉ የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች እንዲሟሉ በማድረግ ማዕከሉ በሚቀጥለው ዓመት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው ማዕከሉ በተለይ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በራስ አቅምና ፍላጎት በማድረግ የተሻለ ልማትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡ በተለይ ውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የድሬዳዋ ምሁራን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውና እንቅስቃሴ መጀመራቸው ማዕከሉ ድሬዳዋን የምስራቁ የንግድና የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን በጥናት ለመደገፍ ይረዳል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም