ዲላ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ያከናወናቸው ስራዎች የሚጠበቀውን ውጤት አላመጡም - ባለድርሻ አካላት

52
ዲላ ኢዜአ መስከረም 28 ቀን 2012 የዲላ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት የሚጠበቅበትን ውጤታማ ስራ አለማከናወኑን ባለድርሻ አካላት ገለፁ። ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀው ማህበረሰብ አቀፍ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት በወቅቱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ከ23 ዓመት በላይ ቢሆነውም የህብረተሰቡን ችግር በሚፈቱ ምርምሮችና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት የሚጠበቅበትን ውጤታማ ስራዎች አላከናወኑም። የጌዴኦ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወይዘሮ የምስራች ገመዴ ዩኒቨርሲቲው  በግብርናው ዘርፍ የሰብል ምርታማነትን ለማሻሻል የሚረዱ በሽታን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን በማላመድና የእንሰሳት እርባታን ለማሻሻል ያደረጋቸው ጅምር ስራዎች ቢኖሩም የሚፈለገውን ውጤት አላመጡም ። ዝርያዎቹን በማስፋፋት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ከማድረግና የእውቀት ክፍተቱን ከመሙላት አኳያ ያከናወናቸው ስራዎች ውስን መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። በተለይም ዞኑ በቡና አምራችነቱ የሚታወቅ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲው ልማቱን ለማስፋፋት ምርታማነቱን ለማሳደግና ጥራቱን ለማስጠበቅ ያከናወናቸው ተግባራትም ውስን መሆናቸውን ተናግረዋል ። በየዓመቱ በአንድ ወረዳ ብቻ ከ4 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች ለተከላ ቢያስፈልጉም ዩኒቨርሲቲው ዞኑን ጨምሮ ለአጎራባች አከባቢዎች የሚያሰራጫቸው የተሻሻሉ ዝርያቸው ችግኞች ከ100 ሺህ እንደማይበልጡ ለአብነት ጠቅሰዋል። መንግስት በዞኑ ያለውን የፍራፍሬ ሃብት ጥቅም ላይ ለማዋል የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢዱስትሪ ፓርክ ግንባታ እያካሄደ ቢሆንም በዩኒቨርሲቲው በኩል ግብአት የሚሆኑ ምርቶችን ለማስፋፋትና ለማሻሻል ያሳየው ተነሳሽነት አለመኖሩንም ጠቁመዋል። እንደ አፈጉባኤዋ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በሽታን የሚቋቋሙና የተሻሻሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በማላመድና ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡ በምዕራብ ጉጂ ዞን የዓባያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አየለ ዴንባ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በወረዳው የተጎዱ አካባቢዎችን ወደ ቀድሞ ገጽታቸው ለመመለስ የጀመራቸው ጥረቶች ቢኖሩም  የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጡ ተናግረዋል። መንግስት የአካባቢውን አርሶ አደር  ለመጥቀም ከፍተኛ ሃብት በመመደብ መስኖ ግድብ ቢገነባም በአጠቃቀም ችግር የሚፈለገው ውጤት አለመምጣቱን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው ዩኒቨርሲቲው በመስኖ አጠቃቀም ዙሪያ ለአርሶ አደሩ የክህሎት ስልጠናና የሙያ ድጋፍ ሊሰጥ እንደሚገባ አመላክተዋል ። የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሪክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ክብሩ አለሙ ዩኒቨርሲቲው በጌዴኦ፣ በምዕራብ ጉጂና ሲዳማ ዞኖች በከፊል የተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል ። በዩኒቨርሲቲው እየተከናወኑ ያሉ ሰራዎች ችግር ፈች እንዲሆኑና ውጤት እንዲያስመዝግቡ የጋራ ጥረት ይጠይቃል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ወደ ህብረተሰቡ እንዲወርዱና የእውቀት ሽግግር እንዲፈጠር ከማድረግ አኳያ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል ። የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ በበኩላቸው ባለፉት አመታት በተቋሙ የነበሩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በማህበረሰብ አገልግሎት የተፈለገው ውጤት እንዳይመዘገብ አሉታዊ ተጽኖ መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል ። ዩኒቨርሲቲው የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የምርምር ማዕከል ከማቋቋም ጀምሮ የተሻሻሉ ዝርያዎቸን ለማላመድ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል  ተናግረዋል ። የጌዴኦ ህዝብ የሚታወቅበትን የአከባቢ ጥበቃ ባሀል ለማጎልበት የእጽዋት ጥበቃና የኢኮ ቱሪዝም ማዕከል ለማቋቋም የተጀመሩ ስራዎችም ትኩረት እንደሚሰጣቸው ገልጸዋል። እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በመድረኩ የተነሱ ገንቢ ሃሳቦችን በመውሰድ በቀጣይ አምስት ዓመት የማህበረሰብ አገልግሎቱን የስትራቴጅክ እቅድ አካል በማደረግ ይሰራል ። በምክክር መድረኩ ከጌዴኦ ዞን፣ ከምዕራብ ጉጂ አባያ ወረዳና ከሲዳማ ዞን ዳራ ወራዳ የተወጣጡ ወደ 200 የሚሆኑ ባለ ድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም