አመልድ ከ320 በላይ አነስተኛ የመስኖና የውሃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለአገልግሎት አበቃ

111
ባህር ዳር  ኢዜአ መስከረም 28/2012 የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት /አመልድ/ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች 323 አነስተኛ የመስኖና የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱን ገለጸ። ለአገልገሎት የበቁት ድርጅቱ በመደበው 126 ሚሊዮን ብር በጀት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2019 ከጀመራቸው ግንባታዎች መካከል ነው። በድርጅቱ የመስኖ፣ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶች አስተባባሪ አቶ ቀፀላ ንጉሴ ለኢዜአ እንዳሉት ፕሮጀክቶቹ የተገነቡት በክልሉ ድርቅ በተደጋጋሚ  በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ነው። በዚህም በሰሜን ወሎ፣ ዋግህምራ፣ ኦሮሞ ብሄረሰብ፣ ደቡብና ሰሜን ጎንደር ዞኖች የማህበረሰብ ኩሬዎች ጨምሮ ከሚያስገነባቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 24 ተጠናቀው ለአገልግሎት በቅተዋል። ለአገልግሎት የበቁት እነዚህ ፕሮጀክቶች 312 ሄክታር መሬት  በመስኖ በማልማት አንድ ሺህ 300 የሚሆኑ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው። በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከተጀመሩት 322 የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ውስጥ ደግሞ  299 ተጠናቀው  ለህብረተሰቡ አገልግሎት መዋላቸውን አስተባባሪው ተናግረዋል። የውሃ ፕሮጀክቶቹ ከ11 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ በማድረግ ቀደም ሲል የነበረባቸውን እንግልት፣ የጊዜና የጉልበት ብክነት  እንደሚያስቀር አመልክተዋል። እንደ አስተባባሪው ገለጻ ያልተጠናቀቁ አነስተኛ የመስኖ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን እስከ መጪው ታህሳስ ወር በማጠናቀቅም ተጨማሪ ከ91 ሺህ 500 ላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ይሆናሉ። አርሶ አደር ምስጌ መልኬ በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ የ031 ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ  "አመልድ በደረሞ ወንዝ የመስኖ ግንባታ በማካሄዱ እኔን ጨምሮ የአካባቢው አርሶ አደሮች የመስኖ ልማቱ ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል" ሲሉ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል። ቀደም ሲል የክረምት ወቅት ዝናብን ጠብቀው የሚያለሙት  ሰብል  ዓመታዊ ቀለባችንን ለመሸፈን ይቸግራቸው እንደነበር አስታውሰዋል። ባለፈው ዓመት የበጋ ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ሄክታር የሚጠጋ መሬቴ ላይ ቀይ ሽንኩርት በማልማት ያገኙትን አስር ኩንታል ምርት ለገበያ አቅርበው በመሸጥ ከስምንትሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ  እንዳሉት በ2011 የመኸር ወቅት ከሰብል በተጓዳኝ  ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያና ካሮት  በማልማት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ ነው። ድርጅቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ ከገነባላቸው ወዲህ የነበረባቸው ችግር መቃለሉን የተናገሩት ደግሞ በምስራቅ ጎጃም ዞን ማቻክል ወረዳ የአማሪ የወበሽ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ አበቡ ስማቸው ናቸው። በዚሁ ወረዳ የየነር ቀበሌ አርሶ አደር ጋሻዬ ዘሪሁን በበኩላቸው ቀደም ሲል አማራጭ ስላልነበራቸው   ንፅህናው ያልተጠበቀን ወራጅ ውሃ  በመጠቀም የውሃ ወለድ በሽታ ይገጥማቸው እንደነበር ገልጸዋል። አመልድ በአቅራቢያቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃቱ ችግራቸው መቃለሉን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም