የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለት ጥናቶች አዘጋጀ

129
አዲስ አበባ ሰኔ 9/2010 በቅጣት አወሳሰን ላይ ፍትሃዊነትን የሚያረጋግጥ የወንጀል ቅጣት አወሳሰ መመሪያ ማኑዋል ጥናት ማጠናቀቁን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። በተመሳሳይ የዳኝነት ስነ ምግባርና ዲሲፕሊን ደንብ ማሻሻያ ጥናትም ተጠናቋል ነው ያለው። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ፀጋዬ አስማማው ለኢዜአ እንደተናገሩት የወንጀለኛ መቅጫ ህግ የቅጣት አፈፃፀም ቢወጣለትም ለአንድ ወንጀል የተቀመጠው የቅጣት መጠን ክልል መራራቅ ለዳኞች ግላዊ አተያይ ተጋላጭ ሆኗል። ለምሳሌ ለአንድ የወንጀል ቅጣት ከአምስት እስከ ሃያ ዓመት የሚል የቅጣት አወሳሰን ቢኖርና በነዚህ መካከል ያለው የውሳኔ አሰጣጥ እንደ ወንጀሉ ቅለትና ክብደት ታይተው የሚሰጡ ቢሆንም "ህግ ያልደነገጋቸው ናቸው" ብለዋል። በዚህም ሳቢያ የቅለቱና የክብደቱ መጠን በዳኛው ግላዊ አተያይ መሰረት የሚዳኝ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ ደግሞ በአንድ የወንጀል ጥፋት ላይ ተመሳሳይ ያልሆነ ውሳኔ እንዲኖር ምክንያት ሆኖ ቆይቷል ነው ያሉት። አንድ ዓይነት ወንጀል ፈጽመው በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ዳኝነት ያገኙ ወንጀለኞችም የቅጣት መጠናቸው በዚህ ምክንያት በመለያየቱ የግልፅነት ችግር ሆኖ መቆጠርም ጀምሮ ነበር ብለዋል አቶ ፀጋዬ ። ይህም በተገልጋዮች ዘንድ የፍትሃዊነት ጥያቄ ማስነሳቱ ነው የተገለፀው። ለሶስተኛ ጊዜ የሚሻሻለው ይህ የወንጀል ቅጣት አወሳሰን ረቂቅ መመሪያ እነዚህን መራራቆች በማቀራረብና እንደ ወንጀል አፈፃፀሙ ክብደትና ቅለት የታወቀና ሁሉም ዳኞች አንድ አይነት አተያይ ኖሯቸው የቅጣት መጠን ለመጣል ያሚያስችል መሆኑን ነው ምክትል ፕሬዝዳንቱ የሚገልጹት። ማሻሻያ ማኑዋሉ ደረጃ ላልወጣላቸው የወንጀል ቅጣቶችም ደረጃ የማውጣት ተግባርም ተከናውኖበታል። ሌላኛው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ተጠናቆ ለውይይት በዝግጅት ላይ የሚገኘው የተሻሻለ የዳኝነት የስነ ምግባር ደንብ የዳኞችን የስነ ምግባር ሁኔታ ዓለማቀፋዊ ደረጃ ኖሮት እንዲመራ ለማድረግ በማሰብ የተሻሻለ ደንብ ነው። ደንቡ ፍትህን ከማስፈን አንፃር የዳኞችን ተጠያቂነት በማሳደግ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የሚያስችል መሆኑንም ነው አቶ ፀጋዬ  የተናገሩት። ሁለቱም የማሻሻያ ጥናቶች ከያዝነው የሰኔ ወር ጀምሮ በዳኞችና በሚመለከታቸው አካላት ተመክሮበት ወደ ተግባር እንደሚገባም ለማወቅ ተችሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም