የጤና ሚኒስቴር መለያ ዓርማውንና መሪ ቃሉን ቀየረ

62
መስከረም 27/2012  የጤና ሚኒስቴር ለረጅም ዓመታት ሲጠቀምበት የቆየውን መለያ ዓርማና መሪ ቃሉን መቀየሩን ዛሬ ይፋ አደረገ። ሚኒስቴሩ ላለፉት 70 ዓመታት የኀብረተሰቡን ጤና በመጠበቅ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሚናውን ሲወጣ ቆይቷል። ተቋሙ የሚከውናቸውን ተግባራት በአዳዲስ አሰራሮችና ለውጥ ለማገዝ ባቀደው መሰረት መለያ ዓርማውን በአዲስ መልክ ያስተዋወቀ ሲሆን መሪ ቃሉም ''የዜጎች ጤና ለአገር ብልጽግና'' የሚል ሆኗል። ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሰሃረላ አብዱላሂ እንደተናገሩት የዓርማው ለውጥ የሚኒስቴሩን ራዕይና ተልዕኮ ከግምት ያስገባ ነው። እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ ተቋሙ በጀመራቸው የለውጥ ስራዎች ኀብረተሰቡ የሚያማርርባቸውን ችግሮች ለመፍታት እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ለህክምና መሳሪያ ጥገና የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ላይ መስራት ከለውጥ ተግባራት መካከል መሆኑን ጠቅሰው አገልግሎት አሰጣጡን ማዘመንም 'ዋና የትኩረት አቅጣጫ ነው' ብለዋል። እንደ ሚኒስትር ዴታዋ የህክምና ጥራት ጉዳይ ቁልፍ እንደመሆኑ 24 የመንግሥት ሆስፒታሎች ላይ አገልግሎት አሰጣጡን የማዘመንና ጥራት የማስጠበቅ ተግባራት ተጀምረዋል።                    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም