የኢትዮጵያውያን መሃንዲሶች የባቡር ቴክኖሎጂ እውቀት እየዳበረ ነው

100

አዲስ አበባ መስከረም  27/2012 በኢትዮጵያ በውጭ አገራት ኩባንያዎች እየተከናወኑ ያሉት የባቡር መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የቴክኖሎጂ ሽግግርን እውን በማድረግ አወንታዊ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን በፕሮጀክቶቹ የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያን መሃንዲሶች ገለፁ።

ኢትዮጵያ እያከናወነች ባለው መሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታ የተሻለ አቅምና የቴክኖሎጂ ያላቸው ዓለም አቀፍ የግንባታ ተቋራጮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዓለም አቀፍ ተቋማቱ ግንባታውን ከማከናወን ባሻገር ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እውቀትን በማሸጋገር ረገድ አወንታዊ ሚናቸውን እየተወጡ ነው።

ይህም ኢትዮጵያዊያኑ መሐንዲሶች በቀጣይ በአገራቸው በራስ አቅም ስራዎችን ለማከናወን እንደሚያግዛቸው ታምኖበታል።

"ያፒ መርከዚ" የተሰኘው የቱርክ ኩባንያ በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ተቋማት እየተገነቡ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል የአዋሽ- ኮምቦልቻ-ወልዲያ/ሃራ ገበያ የባቡር መስመር ግንባታን በማካሄድ ላይ ነው።

ከዚህ ኩባንያ ጋር እየሰሩ ያሉት ኢትዮጵያውን ባለሙያዎች ለኢዜአ እንደገለፁት ኩባንያው በሚያካሄደው ፕሮጀክት በመሳተፋቸው የዘርፉን እውቀትና ቴክኖሎጂ እየቀሰሙ ነው።

እንደ ባለሙያዎቹ ገለጻ ከውጭ ባለሙያዎች ጋር በጋራ በሚያከናውኑት ሥራ በቀጣይ አገሪቱ ለምታከናውነው የባቡር መሰረተ ልማት የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማድረግ ላይ ናቸው።

የባቡር መስመር ባለሙያው መካኒካል ኢንጅነር አስራት ብርሃኑ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተማረውን ትምህርት ከዓለም አቀፍ የዘርፉ ሙያተኞች ጋር በመሥራቱ በተግባር ልምምድ ክህሎት እንዳገኘ ተናግሯል።

ባለሙያዎቹ ባገኙት ልምድ የባቡር መስመሩ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በራሳቸው የመስራት አቅም ማጎልበታቸውንም አስረድተዋል።

የምህንድስና ባለሙያው ሃይለማሪያም አሰፋ በበኩሉ የባቡር ቴክኖሎጂን ዓለም ከደረሰበት ዘመናዊ የፈጠራ ደረጃ ጋር ለማስኬድ ከተለያዩ አገር ከመጡ ሙያተኞች ጋር በመስራቱ የተለያዩ ልምዶችን ቀስሟል።

ኢንጅነር ሻሎም አሽሮም በፕሮጀክቱ መሳተፉ በባቡር መሰረተልማት ቀጣይ ስራዎችን በተሻለ መልኩ ለማከናወን የሚያስችል ልምድ እንዲያገኝ ነው ያስረዳው።

እየሰራበት በሚገኘው የባቡር ድልድይ ግንባታ ዘርፍም የተለያዩ ቴክኒካል ክህሎቶችን እንዳገኘ ነው የሚናገረው ኢንጅነር ሻሎም።

በአገር ውስጥ ባቡር መጠገን የሚያስችል እውቀት ማግኘቱን የሚናገረው የወርክሾፕ ጥገና መሃንዲስ ተክለብርሃን አበበ፤ በሀገር ውስጥ የባቡር ብልሽት ሲያጋጥም በራሱ ለመጠገን ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

የአዋሽ- ኮምቦልቸ-ወልድያ/ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር አብዱልከሪም መሃመድ እንደሚሉት፤ በፕሮጀክቱ በከፍተኛ ባለሙያነት እየሰሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች በዚህ ፕሮጀክት ከአምስት ዓመታት በላይ ሠርተዋል።

ባለሙያዎቹ ከቆይታቸው አንጻር በቂ ክህሎት ያገኙና በቀጣይ በራሳቸው አገልግሎቱን ማስኬድ የሚችሉበት ደረጃን መቀዳጀታቸውን አረጋግጠዋል።

በአዋሽ- ኮምቦልቸ-ወልድያ/ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት በአጠቃላይ በተለያየ የሙያ ዘርፍ 2 ሺህ 500 ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ከሠራተኞቹም መካከል ከ40 በላይ የሚሆኑት ሠራተኞች የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውና ከፍተኛ ባለሙያዎች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም