በጅማ ዞን በ16 ሚሊዮን ዶላር የሚካሄድ የጤና አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ተጀመረ

60
ጅማ (ኢዜአ) መስከረም 27 ቀን 2012 በኔዘርላንድስ መንግስት ድጋፍ በጅማ ዞን የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ተግባራዊ የሚደረግ የ16 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ትላንት በይፋ ተጀመረ። ፐርፎርማንስ ቤዝ ፋይናንሲንግ (ፒ ቢ ኤፍ ) የተሰኘው ፕሮጀክት ይፋ የተደረገው በአጋሮ ከተማ ነው። በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ምክትል አምባሳደር ቲጂስ ዎንደስትራ በወቅቱ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በአራት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚካሄድ ነው ። የጤና ተቋማትን ማስፋፋት፣ በቁሳቁስ ማደራጀት፣ የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ማዘመን፣ ለባለሙያ ስልጠና መስጠትና የህረተሰቡን ግንዛቤ የማዳበር ስራዎች በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል ። ለፕሮጀክቱ ትግበራ የተመደበው ገንዘብ የሚለቀቀው በየዓመቱ በሚከናወኑ ስውራዎች አፈጻጸምና በህብረተሰቡ የአገልግሎት እርካታ መሰረት እንደሚሆን ገልጸዋል ። የጅማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልከሪም ሙሉ በፕሮጀክቱ የሚከናወኑ ተግባራት የዞኑን የጤና አገልግሎት የሚያሻሽሉ መሆናቸውን ነው የገለጹት። ቀልጣፋ የጤና አገልግሎት ለመስጠትና የሥራ ባህልን ለማሻሻል ፕሮጀክቱ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች የሚደረገውን ድጋፍ በአግባቡ ለመጠቀም በትጋት እንዲሰሩ አስገንዘበዋል። በፕሮጀክቱ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርዓት ላይ የፌደራል ጤና ጥበቃ ተወካዮች፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ የሥራ ኃላፊዎችና የኔዘርላንድስ ቆንስላ ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም