ብሔራዊ ቡድኑ ለቻን ማጣሪያ ጨዋታ ነገ በባህርዳር ዝግጅቱን ይጀምራል

116
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 27/2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር /ቻን/ ከሩዋንዳ አቻው ጋር ላለበት ግጥሚያ ዝግጅቱን ነገ በባህርዳር እንደሚጀምር ተገለጸ። ቡድኑ ከዩጋንዳ አቻው ጋር በመጪው እሁድ የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግም ታውቋል። ስድስተኛው የቻን ውድድር በጥር 2012 ዓ.ም በካሜሮን አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን ተሳታፊ አገራት የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጥቅምት 8 ቀን 2012 ዓ.ም በኪጋሊ 30 ሺህ ሰው በሚያስተናግደው የአማሆሮ ብሔራዊ ስታዲየም የቻን ሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከሩዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል። ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው። የቡድኑ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ባለፈው ሳምንት ለመልሱ ጨዋታ ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ዛሬ ወደ ባህርዳር እንደሚያቀኑና ከነገ ጀምሮ በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ልምምድ እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ባህሩ ጥላሁን ለኢዜአ ገልጸዋል። ብሔራዊ ቡድኑ ከርዋንዳ ጋር ላለበት ጨዋታ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ የወዳጅነት ጨዋታ ለማካሄድ ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር በተደረገ ግንኙነት ከዋልያዎቹ ጋር እንደሚጫወት መግለጹን ተናግረዋል። በዚሁ መሰረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የዩጋንዳ አቻው እሁድ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሠዓት የወዳጅነት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ከነገ በስቲያ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን አጠናቆ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም ወደ ርዋንዳ ኪጋሊ ያመራል ብለዋል። ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የሚጫወተውና በአሰልጣኝ ቪንሰንት ማሻሚ የሚሰለጥነው የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለጨዋታው ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ጥቅምት 3 ቀን 2012 ዓ.ም ከታንዛኒያ አቻው ጋር እንደሚጫወት ታውቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደርሶ መልስ ውጤት የሩዋንዳ አቻውን ካሸነፈ በካሜሮን በሚካሄደው የቻን የእግር ኳስ ውድድር ይሳተፋል። ዋልያዎቹ በሐምሌ 2011 ዓ.ም ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር የቻን የማጣሪያ ጨዋታ የጅቡቲ አቻቸውን 5 ለ 3 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፈዋል። በካሜሮን ለሚካሄደው ውድድር በሰሜን ዞን፣ በምዕራብ ዞን ኤ፣ በምዕራብ ዞን ቢ፣ በማዕከላዊ ዞን፣ ማዕከላዊ ምስራቅ ዞን እና ደቡብ ዞን ተከፋፍሎ ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ማጣሪያ እየተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። በሁለተኛው ዙር በሚካሄዱ የማጣሪያ ጨዋታዎች የደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊ የሚሆኑ 15 ብሔራዊ ቡድኖችና አዘጋጇ አገር ካሜሮን በድምሩ 16 ቡድኖች በቻን ውድድር ይሳተፋሉ። የቻን የእግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ በ2009 በኮትዲቯር አስተናጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋናን በመርታት አሸናፊ ሆናለች። እስካሁን በተካሄዱት ውድድሮች ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሁለት ጊዜ እታሸንፍ ቱኒዚያ፣ ሊቢያና ሞሮኮ አንድ አንድ ጊዜ ውድድሩ ያሸነፉ ናቸው። የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር /ቻን/ በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበትና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም