በየዘርፉ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን ለማሳካት ይረዳል

58
መስከረም 27/2012  ኢትዮጵያ በየዘርፉ እያስመዘገበችው ያለው ለውጥ ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን ለማሳካት አመላካች መሆኑን የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ገለፀ። አካዳሚው ላለፉት ሁለት ዓመታት በሥነ ህዝብና ልማት ዙሪያ ሲሰራ የቆየው ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ መርሀ ግብር ትናንት ምሽት በአዲስ አበባ አካሂዷል። አገሪቱ በጤና፣ በትምህርት፣ በቤተሰብ ዕቅድ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በመልካም አስተዳደር ዘርፎች እያስመዘገበችው ያለው ለውጥ የሥነ ህዝብ ትሩፋቶችን ለማሳካት አመላካች መሆኑን ገልጿል። የአካዳሚው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጽጌ ገብረማርያም እንደገለፁት ኢትዮጵያ እስካሁን በየዘርፉ ያስመዘገበችው ለውጥ ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን ልታሳካ እንደምትችል አመላካች ነው። አገሪቱ ወሊድና ሞትን በመቀነስ በኩል አበረታች ለውጥ እያሳየች መሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ በዚህም የሕዝቧ የዕድሜ አወቃቀር ከፍተኛ ቁጥር ወዳለው አምራች ኃይል እየተቀየረ፣ ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋት የሚገኝበትን የዕድል መስኮትም እየከፈተ መሆኑን ተናግረዋል። አገሪቷ በተለያዩ ዘርፎች ያሳየቻቸው ለውጦች የሚበረታቱ ቢሆንም፤ በየዘርፉ ፈጣንና ዘላቂ ምላሽ የሚያሻቸው ችግሮችም እንዳሉ ጠቁመዋል። እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት በሕዝብ ጥያቄዎችና ዓላማዎች ላይ የተመሠረተ አሳታፊና ተጠያቂ የሆነ፤ በመረጃ ላይ የተደገፉ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ፣ ለመተግበርና ጥራት ያላቸው የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ብቃትና ቁርጠኝነት ያለው አስተዳደር ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል። ሥነ ሕዝባዊ ትሩፋትን ለማሳካት ጤናማ፣ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ ዜጋ መፍጠር፣ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ኢኮኖሚን ማጠናከርና መልካም አስተዳደር ላይ መሥራት እንደሚያሻም አክለዋል። ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ ማድረግ እንዲሁም ይህን የሚገቱ የተሳሰሩ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በተቀናጀ ሁኔታ በአፋጣኝ መፍታት እንደሚገባም አስረድተዋል። አገሪቱ ይህን ካደረገች በማይተኩ ሐብቶቿ የሥነሕዝብ ትሩፋትን የምታሳካበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም