የፌዴራል ፍትህ ተቋማት በቅንጅት ለመስራት የመሰረቱት ፎረም ለውጥ አምጥቷል ተባለ

129
    አዲስ አበባ ሚያዝያ 29/2010 የፌዴራል ፍትህ ተቋማት ፎረም መስርተው በቅንጅት መስራት መቻላቸው ለውጥ ማስገኘቱን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ። 8ኛውን አገር አቀፍ የፍትህ ሳምንት አስመልክቶ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 5 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ የፌዴራል ፍትህ ተቋማትን ያሳተፈ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ ተከፍቷል። በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዝዳንት አቶ ዳኜ መላኩ እንደተናገሩት፤ የፌዴራል ፍትህ ተቋማት በ2002 ዓ.ም በጋራ ያቋቋሙት ፎረም በቅንጅት በመንቀሳቀስ ተቋማቱ ለጋራ ችግሮቻቸው የጋራ መፍትሄ የሚሰጡ አሰራሮችን በመዘርጋት አዎንታዊ እገዛ አድርጓል። ፎረሙ የፌዴራል ፍርድ ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች፣ የአዲስ አበባና የፌዴራል ፖሊስና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግን ያካተተ ነው። በፍርድ ሂደት ላይ የቀጠሮ መጓተት መቀነስ፣ የህጻናት መብትና ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል የቅብብሎሽ ስርዓት በመዘርጋት፣ የሰው ሀይል አቅም መጎልበትና ለተጠርጣሪዎች ጉዳይ የተናበበ ምላሽ መስጠት የፎረሙ መመስረት ያበረከተው አስተዋጽኦ እንደሆነ ለአብነት ጠቅሰዋል። ሆኖም የፍትህ አካላት የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍና፣ ተደራሽነትና ጥራት በሚፈለገው ደረጃ አለመድረሱን ከተገልጋዮች በየጊዜው የሚነሱ ቅሬታዎች የሚያረጋግጡ መሆኑን ገልጸዋል። 'የፍትህ አካላቱም በተለይም ካለፈው አመት ጀምሮ የህዝቡን አስተያየት መነሻ በማድረግ ለሚነሱ ችግሮችና ቅሬታዎች በአመለካከትና በአሰራር የተደገፈ መፍትሄ ለመሰጠት ወደ ስራ ገብተናል' ብለዋል። በስራ መደራረብ ሳቢያ የሚፈጠረውን የቀጠሮ መጓተት ችግር ለመቀነስ ከባለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ የዳኞችን ቁጥር ለማሳደግ የዳኞች ምልመላ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል። ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮችን ክብደትና ቅለት ከግምት ውስጥ በማስገባት ውሳኔ የሚሰጥበትን ቀን የሚያስቀምጥ የቀጠሮ ፖሊሲ ስርዓት ጥናት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣዩ አመት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ያለው የፍትህ ሳምንት ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች በፍትህ ተቋማት ላይ ያሉ ክፍተቶችን እንዲገልጹና ቅሬታቸውንና ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ እድል የሰጠ መሆኑንም አንስተዋል። ይህም በዜጎች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ለመቀነስና የፍትህ ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም