የወርቅ የግብይት ማዕከላትን ማስፋፋት ተግባራት ተጀምሯል - ሚኒስቴሩ

72
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 26/2012 የወርቅ የግብይት ማዕከላትን ማስፋፋት ተግባራት መጀመሩን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ። በሕገ ወጥ ማዕድን ንግድና ኮንትሮባንድ ላይ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ሚኒስቴሩ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር መግለጫ ሰጥቷል። ኢትዮጵያ ከጌጣጌጥ ማዕድናት የምታገኘው ገቢና ምርት ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ እየቀነሰ መጥቷል። የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያሳየው በተለይ ወርቅ በ2004 ዓ.ም 445 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ይገኝ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ገቢው ወደ 32 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሏል። ይህም አገሪቷ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ ሲሆን የኃብት መቀነስና የገንዘብ ግሽበትን እያስከተለ እንደሆነ ነው የተገለጸው። በሚኒስቴሩ የገበያ ልማት፣ ትስስርና ትንበያ ዳይሬክተር በትሩ ኃይሌ እንደተናገሩት፤ በ2012 ዓ.ም ሁለት ወራት እንኳን ከተለያዩ ወርቅ አምራች አካባቢዎች ለብሄራዊ ባንክ ገቢ የተደረገው ወርቅ 150 ኪሎ ግራም ብቻ ነው። ሕገ ወጥ የማዕድን ንግድ ቁልፍ ችግር መሆኑን ጠቅሰው መፍትሄ ለማበጀትም ሚኒስቴሩ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከብሄራዊ ባንክ ጋር በጥምረት እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ በተለይ ወርቅ አምራች አካባቢዎች ገበያ በቅርበት አለማግኘታቸው ለኮንትሮባንድ መባባስ አስተዋጽኦ ያበረከተ በመሆኑ የግብይት ማዕከላት የማቋቋም ሥራዎች እየተከናወኑ ነው። ለአብነትም በአፋር ክልል ኮነባ የተባለ ቦታ ላይ የወርቅ የግብይት ማዕከል እየተቋቋመ ነው ሲሉ አክለዋል። በጋምቤላ፣ ሀዋሳ፣ ዲማ በተባሉ ቦታዎች ላይ የወርቅ የግብይ ማዕከላት እንደተቋቋመም ገልጸዋል። ሕገ ወጥ የማዕድናት ንግድን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ገቢራዊ እየተደረጉ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ኅብረተሰቡ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴን የሚያጋልጥበት ነጻ የስልክ መስመር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመዋዋል ስራ ላይ መዋሉን አስታውቀዋል። በዚሁ መሰረት በነጻ የስልክ መስመር 6038 ላይ በመደወል ኅብረተሰቡ ሕገ-ወጦችን እንዲያጋልጥም ጥሪ  አቅርበዋል። ''ማዕድናት የሚመረቱባቸው አካባቢዎች በተለይ ወረዳና ቀበሌዎች የማዕድን ኮንትሮባንድን በመከላከል ረገድ ትርጉም ያለው ሥራ ሊከውኑ ይገባል'' ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሚኒስቴሩ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። የማዕድን ሚኒስቴር ውል ፈጽመው በውሉ መሰረት የማይሰሩ ኩባንያዎች እንዲሁም ውላቸውን በተገቢው ጊዜ እያደሱ የማይሰሩት ላይ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነም አብራርተዋል። በጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ተገዥነት ዘርፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አሸናፊ ባሳ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በነጻ የስልክ መስመር የሚደርሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢዎች ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል። ህገ ወጥ ነጋዴዎች ወደ ህግ የሚቀርቡበትን ሁኔታ ዜጎች መደገፍ እንደሚኖርባቸውም አመልክተዋል። በቅርቡ 8 ነጥብ 7 ኪሎግራም ወርቅ ቶጎጫሌ ላይ መያዙን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም