በኢትዮጵያ የዲጂታል እውቀትና ክህሎትን ለማስረፅ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ቀጥለዋል

99
መስከረም 26/2012 በኢትዮጵያ የዲጂታል እውቀትና ክህሎትን ለማስረፅ ማዕከላትን ከማስፋት በተጨማሪ ግንዛቤን ማሳደጊያ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ። ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የዓለም አቀፍ የአስትሮኖሚካል ኅብረት ሲምፖዚየም ማካሄድ ጀምራለች። ከዛሬ መስከረም 26 ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቀጥለው ሲምፖዚየም ላይ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ተመራማሪዎች እየተሳተፉበት ይገኛሉ። በዚሁ ወቅት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስን ከልማት ጋር አስተሳስራ ለመስራት ከፖሊሲና ስትራቴጂ ጀምሮ እየተሰራ ነው። አገሪቱ በስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላት የቅርብ ጊዜ ታሪክ ቢሆንም ባለፉት አራት አመታት እየታዩ ያሉ መልካም ጅማሮዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። አገሪቱ በታህሳስ ወር መጀመሪያ ወደህዋ የምታመጥቀው ሳተላይት ከነዚህ ተግባራት ውስጥ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ዘርፉን ለማጠንከር ከሚሰሩ ስራዎች መካከል የሳይንስ እውቀትን በኀብረተሰቡ ውስጥ ማስረፅ አንዱ መሆኑንም አስረድተዋል። አገሪቱ ካላት ህዝብ ውስጥ የዲጂታል አሰራርና መሳሪያዎችን መገንዘብና መጠቀም የሚችለው ምን ያህል እንደሆነ ለመዳሰስ በተካሄደ ጥናት ያለው ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ማሳየቱንም ገልፀዋል። የዲጂታል ክህሎትና እውቀትን ለማስረፅ የሳይንስ ካፌዎችን የመገንባት፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የቴክኖሎጂ ኢንኪዩቤሽን ማዕከላትን ማስፋፋትና የኢኖቬሽን ማዕከላትን የማስፋት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል። የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና አይሲቲ ኤጀንሲ በሁሉም ክልል እንዲቋቋምና አሰራርና አደረጃጀቱን እስከ ትምህርት ቤቶች ድረስ በተዋረድ እንዲዘረጋ መደረጉንም እንዲሁ አንስተዋል። የሳይንስ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚዲያዎችም ወደ ስራ እንዲገቡ ለማድረግ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸዋል። እየተካሄደ ያለው ሲምፖዚየም  ከአስትሮኖሚ ጋር ተያያዥ የሆኑ በርካታ ምርምሮች፣ ሳይንሳዊ ግኝቶች እንዲሁም ከአገሮች ልማት ጋራ ያለውን ግንኙነት የሚያመላክቱ ውይይቶች የሚደረጉበት በመሆኑ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ በበኩላቸው ሲምፖዚየሙ የኢትዮጵያ ተመራማሪዎች በአለም ላይ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው የሚያስገነዝብና ከልምምድ ልውውጥ ባሻገር ግንኙነትን ለመፍጠር የሚያስችላቸው መሆኑን ገልፀዋል። ለአገሪቱ የገፅታ ግንባታና የኢኮኖሚ አስተዋፅኦ እንዲሁም ለቱሪዝም ፋይዳ እንዳለውም አብራርተዋል። ኢንስቲትዩቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በዘርፉ ትምህርት እየሰጠ መሆኑንና በምርምር ላይም ስራዎችን እየከወነ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በቅርቡ ወደህዋ ከምታመጥቀው ሳተላይት በተጨማሪ በሶስት አመት የሚጠናቀቅ የኮሙኒኬሽን ሳተላይት ስራ እንዳለና ሌሎች የተጀመሩ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ሲምፖዚየሙ ከሁለት አመት በፊት በተደረገ ውድድር ኢትዮጵያ ሊደረግ የተወሰነ መሆኑን የገለፁት በኢንስቲትዩቱ የአስትሮኖሚና አስትሮፊዚክስ ምርምር ክፍል ኃላፊና የሲምፖዚየሙ አስተባባሪ ዶክተር ሜሪያና ፖቪች ናቸው። ሲምፖዚየሙ በአገሪቱ ላሉ ተማሪዎች ልምምድ ለመጋራትና ለትብብርና አጋርነት ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል። የተመረጡ 10 የህዝብ ትምህርት ቤቶች በተግባር የታገዘ አስትሮኖሚን የማስገንዘብ ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል።   ለበርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች ስለአስትሮኖሚ ሳይንስ ግንዛቤ የመፍጠር እንዲሁም ለሁለተኛ ደረጃ መምህራንም የሚሰጥ ስልጠና መኖሩ ተገልጿል።   የዓለም አቀፍ የአስትሮኖሚካል ኅብረት 356ኛሲምፖዚየም ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ተመራማሪዎች እየተሳተፉበት ሲሆን በኅብረት በተለያዩ አገሮች የሚዘጋጁ ሲምፖዚየሞች አሉ።   ህብረቱ 100ኛ አመቱን እያከበረ ሲሆን ይህንንም ክብረ በዓል ያከናወናቸውን ስራዎችና ስኬቶች እየገመገመ በተለያዩ ሁነቶች እያከበረ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም