ውሳኔው ሁለቱን ሀገራት ከጸጥታ ስጋት በማላቀቅ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ያስችላል፡- ምሁራን

55
ሀዋሳ/ሶዶ ሰኔ 9/2010 የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ የአልጀርሱን ስምምነት ለመቀበል በቅርቡ ያስተላለፈው ውሳኔ ሁለቱን  ሀገራት ከጸጥታ ስጋት  በማላቀቅ ዘላቂ ሰላምና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአራት ዩኒቨርስቲዎች  ምሁራን ገለጹ፡፡ በወላይታ ሶዶ የስነ ዜጋ ትምህርት መምህር አቶ የዓለምሰው ንጋቱ እንዳሉት ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ወዳጅነትና ማህበራዊ ግንኙነት በማሰብ ስምምኑቱን መቀበል ተገቢ ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን ስምምነት አቋም ይዞ መቀበሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ተቀባይነቱ ተረጋግጦ ከተተገበረ ቀጠናውን ከጸጥታ ስጋት ለማላቀቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አፈጻጸሙ ህዝብን በማመከር ሊሆን  እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የታሪክና የማህበረሰብ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሀበሻ ሽርኮ በበኩላቸው " ስምምነቱ ሁለቱ ሀገራት  የሚገዛንና የመጨረሻ ውሳኔ ነው ብለው ተስማምተው ቢፈራረሙም የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ ዙሪያ በተፈጠረው አለመግባባት በእንጥልጥል መቆየቱ ያስከተለው ጉዳት ብዙ ነው "ብለዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት አሁን ኢትዮጵያ ከወሰደችው እርምጃ ውጭ ሌላ ምርጫ የላትም ፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ ለሽብር የሥጋት ጂኦፖሊቲካዊ ስትራቴጅክ ቀጠና በመሆኑ  ስምምነት ለኢትዮጵያ እና ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን በቀጠናው ለሚገኙ ሌሎችም ሀገራት ሰላምና ደህንነት የሚበጅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ " ባድመ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ነው የሚለውን ሀሳብ ለጊዜው ትተን ሰላም በመፈለግ የተወሰደ እርምጃ መሆኑን በመውሰድ ህዝብ ድጋፍ ማድረግና እርቅ ማውረድ አለበት” ብለዋል፡፡ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ቢያስተላልፉም ሳይፈፀም መቆየቱ ከሁለቱ ሀገራትም ባለፈ በምስራቅ አፍሪካም ላይ ብዙ አሉታ ተፅዕኖ ማሳደሩን የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የህግ ትምህርት ክፍል መምሀር አቶ ማርሸት መሀመድ ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ሳይንስና ስነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዓለምአየሁ አዱኛ በበኩላቸው ስምምነቱ ለወደፊት የእርስበርስ ግንኙነት ለመፍጠር፤ ለጋራ ተጠቃሚነትና አብሮ የመኖር መርህ ለማዳበር የተደረገ እርምጃ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የተወሰደው እርምጃ ኢትዮጵያን በአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል ከማድረግ ረገድ ወቅቱን የጠበቀ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በተመሳሳይ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ መምህር  አቶ ይድነቃቸው ለማ እንደገለጹተ ሁለቱ ሀገራት የአልጀርስ ስምምነቱን ከመፈረም ያለፈ ተግባር ባለመፈጸማቸው ላለፉት ዓመታት በድንበር አካባቢ ያሉ ህዝቦችን በማስጋት  ቆይቷል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ  ስምምነቱን ለመቀበል ያስተላለፈው ውሳኔ የሁለቱን ሀገራት ህዝቦች ለዘመናት ተቆራርጠው የነበሩ ቤተሰቦች የሚገናኙበትን አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ሚኖታ እንዳሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ እህትማማች ሀገራት ናቸው፡፡ ሆኖም ተፈጥሮ በነበረው ግጭት በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ባለመስፈኑ በተለይ በድንበር አካባቢ ያለው ህብረተሰብ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በመቋረጣቸው ተጎጂ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡ ስራ አስፈፃሚው  ይህን ለማስቀረት የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ  በሙሉ መቀበሉ የሚበጅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመፍታት  ሰላማዊ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ   የአልጀርሱን ስምምነት መቀበሉ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ሰላማዊ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር አቶ ኑሪ ከድር ናቸው፡፡ " አካባቢው በሁለቱ ሀገራት መካካል ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት በመሆኑ ስምምነቱ  በመካከላቸው  ያለውን የንግድ ትስስር የሚፈጥርና ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው"ብለዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም