እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በትኩረት ይሰራል - ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

69
መስከረም 26/2012 በበጀት ዓመቱ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት የመቆጣጠር ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመጀመሪያ ስብሰባ  የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ዛሬ ተካሂዷል። የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንቷ የዋጋ ንረቱ በዋናነት የሚስተዋለው በምግብ ሸቀጦች ላይ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን በበቂ መጠን ከውጭ የማስገባት ሥራ ይሠራል። በበጀት ዓመቱ የምጣኔ ሀብት ዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ፍላጎት ተኮር የነበረውን አሠራር አሁን በአመዛኙ ወደ አቅርቦት ተኮር የማሸጋገሩ ስራ በስፋት ተግባራዊ ይደረጋልም ብለዋል። በ2011 በጀት ዓመት የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል በስፋት የተጀመሩ የገቢ ማሰባሰብ ሥራዎች፣ የውጭ ምንዛሬ የማሰባሰብና የውጭ ብድር ጫናን ለማቃለል የዕዳ ማሸጋሸግ የድርድር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል። በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርን መተግበር፣ የማክሮ ኢኮኖሚውን ዘርፍ መዛባት ማስተካከል፣ የኢኮኖሚ መዋቅሮችን ማሻሻል በዓመቱ ከሚከወኑ የምጣኔ ሀብት ማሻሻያ ዋና ዋና ተግባራት መካከል እንደሆኑም ጠቅሰዋል። በተጨማሪም የኢንቨስትመንት ከባቢ ሁኔታን ምቹ ማድረግ፣ የቴሌኮም ዘርፉን ማሻሻልና የሎጂስቲክስ ስርዓትን ማቀላጠፍ የኢኮኖሚ መዋቅር የማሻሻያ ስራዎች ትኩረቶች ናቸው ብለዋል ፕሬዝዳንቷ። የማክሮ ኢኮኖሚውን ጤንነት ማስጠበቅ፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማሳደግና ለዜጎች በቂና አስተማማኝ የስራ ዕድል መፍጠር ስራዎች በበጀት ዓመቱ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ቁልፍ ሥራዎች መሆናቸውንም አክለዋል። “በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የሥራ ፈጠራ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ያወሱት ፕሬዚዳንቷ፤ "በአገር ውስጥና በውጭ አገር ለወጣቶቻችን የሥራ ዕድሎችን የማመቻቸትና የማፈላለግ ተግባራት ይበልጥ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ይሆናል" ብለዋል። በተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች "ወጣቶቻችን ለሥራ ዲሲፕሊን የሚበቃቸውን ሥልጠና ወስደው፣ ተወዳዳሪና ብቁ ሆነው እንዲሠማሩም ይደረጋል” ሲሉም ተናግረዋል። የግብርና ምርታማነትን፣ የአምራችና የቱሪዝም ዘርፉን፣ የውጭ ምንዛሬ ሀብትን ለማስፋትና የአገልግሎት ዘርፉን ለማቀላጠፍ በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል። እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ በተለያዩ ተቋማት በህግና በአሰራር ያሉ እንቅፋቶችን ማስተካከል፣ አሰራርን በቴክኖሎጂ ማዘመንና የሰው ኃይል ብቃት መጨመር ላይ ትኩረት ይደረጋል። በተለያዩ ተቋማት የተበታተኑ አሰራሮችን ለቅልጥፍና በሚያመች መልኩ የማደራጀት ስራም ትኩረት ይሰጠዋል። “ኮንትሮባንድ፣ ታክስ ማጭበርበርንና ታክስ መሰወርን፣ እንዲሁም በሕቡዕ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ወደ ሕጋዊ ሥርዓት በማምጣት ኢኮኖሚውን ወደተሻለ ጤንነት የማሸጋገር የተቀናጀ ሥራ ይከናወናል።” ብለዋል ፕሬዚዳንቷ። የተመረጡ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በከፊልና ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወርና በመንግስትና በግሉ ዘርፍ በአጋርነት የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም