በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት ወደ ሰላም ተመልሷል…የዞኑ አስተዳደር

65
መስከረም 26 /2012 በአማራ ክልል ኤፍራታና ግድም ወረዳ አጣዬ ከተማ ላይ ባልታወቁ ሰዎች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት መረጋጋቱን የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳር አስታወቀ። የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ ዛሬ በሰጠት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት የተፈጠረውን አለመረጋጋት በዘላቂነት ወደ ነበረበት ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ስራዎች በቅንጅት እየተከናወኑ ነው። በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አዋሳኝ ቦታዎች አካባቢ የተከሰተው ግጭት በጸረ-ሰላም ኃይሎች ምክንያት እንጂ በህዝቦች መካከል የተነሳ እንዳልሆነም አስረድተዋል። ከአራት ወራት በፊት በነዚህ አካባቢዎች በተመሳሳይ መልኩ በተከሰተ ግጭት የአጣየና አካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አውስተዋል። "ከዛ ጊዜ ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው የአስፓልት መንገድ ግራና ቀኝ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መቀሳቀስ ክልክል መሆኑ በኮማንድ ፖስት ታውጆ ነበር" ብለዋል። ይሁን እንጂ ሰሞኑን የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሁለት ግለሰቦች አጣየ ከተማ ገበያ ሊገቡ ሲሉ በአካባቢው በጥበቃ ላይ በነበሩ የክልሉ ልዩ ሀይል አባላት ሊያዙ ሲሉ ተኩስ በመክፈታቸው ግጭት መፈጠሩን ተናግረዋል። በእለቱም ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሀይሎች የአጣየን ከተማ ለመውረርና ግጭቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ለማስፋት ያደረጉት ሙከራ በክልሉ ልዩ ሃይል፣ በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ ሰራዊት በተደረገ ጥረት መክሸፉን ገልጸዋል። ይሔንን ተከትሎ በነበረው የተኩስ ልውውጥም አምስት ሰዎች ሲሞቱ አራት መቁሰላቸውን ገልጸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሁለቱም ዞኖች አመራሮች፣ ህዝቡና የሚመለከታቸው አካላት በጋራ እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም