በተያዘው ዓመት ለሁለት የግል የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ ይሰጣል - ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ

53
መስከረም 26/2012 የኢፌዲሪ ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መንግስት በ2012 በጀት ዓመት ለሁለት የግል የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ፈቃድ እንሰሚሰጥ ገለጹ። የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ ፕሬዘዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ የመንግስትን አቅጣጫ አስቀምጠዋል። በኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ለመዘርጋት ዘመናዊና ብቁ ተቋማትን መያዝ ያስፈልጋል ብለዋል። ፕሬዘዳንቷ እንዳሉት፤ ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ተቋማትን ለማዘመን መንግስት የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን በአዋጅ እንዲቋቋም ተደርጓል። በተያዘው የ2012 በጀት ዓመትም ኢትዮ ቴሌኮም በተሰማራበት ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ይሆን ዘንድ የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ እቅድ ተይዟል ብለዋል። በዚህም ሁለት የግሉ ዘርፍ የቴሌኮም ኦፕሬተሮችን አወዳድሮ ፈቃድ በመስጠት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ሶስት ኦፕሬተሮች ይኖሯታል ብለዋል። በዓለም ላይ 65 በመቶ ኢኮኖሚው የሚመነጨው ከአገልግሎት ዘርፍ መሆኑን የገለጹት ፕሬዘዳንቷ፤ በኢትዮጵያም የኢኮሜርስ ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ጥረት ይደረጋል ብለዋል። ፕሬዝዳንት ሳሃለወርቅ በንግግራቸው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሳተላይት በያዝነው ዓመት በታኅሣሥ 2012 ዓ.ም. በቻይና ከሚገኝ የማምጠቂያ ማዕከል ወደ ጠፈር የሚላክ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም ለግብርና፣ ለደን ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ አገልግሎት የሚያስፈልጉትን የሳተላይት መረጃዎች ለመቀበል ይውላልም ብለዋል። ሳተላይቱን በራስ ባለሞያዎች መቆጣጠር የሚያስችል ጣቢያ በአዲስ አበባ እንጦጦ በሚገኘው የስፔስ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት ግቢ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም