በምስራቅ አፍሪካ ከስምንት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል

66
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 26 /2012 በምስራቅ አፍሪካ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ጊዜ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውን የዓለም የፍልሰት ድርጅት ገለጸ። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ በአዲስ አበባ እየመከረ ነው። በኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ተወካይ ማውረን አቺንግ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል። በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት መጀመሪያ 41 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ በየዓመቱም 25 ሚሊዮን ሰዎች ይፈናቀላሉ ብለዋል። ከዚህ ውስጥ በዚሁ የፈረንጆች ዓመት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በምስራቅ አፍሪካ ብቻ ስምንት ሚሊዮን ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ጠቁመዋል። 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ በተለያዩ አገራት በስደተኞች ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ አስረድተዋል። ምንም እንኳን በግጭት ምክንያት የሚፈናቀሉት ሰዎች ቁጥር ቢቀንስም አሁንም በኢትዮጵያና በሶማሊያ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። በግጭቶ መስፋት፣ ለተራዘመ ጊዜ መቆየትና ቶሎ ቶሎ መከሰት ምክንያት በመጪዎቹ ጊዜያትም የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር ይችላል እንደ ተወካይዋ ገለጻ። መፈናቀልን ሊያስከትሉ የሚችሉ ችሮችን ለመፍታት የፖለቲካ ቁርጠኝነት አለመኖርና የአየር ንብረት ለውጥ ችግሩን እንደሚያባብሱትም ተናግረዋል። ያም ሆኖ ተቋማቸው እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የአስተዳደርና የፖሊሲ  መቀናጀት /መናበብ/ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በዘላቂ መፍትሄ ዙሪያ ግንዛቤ ማሳደግና አቅም መገንባት እንዲሁም የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓቱን በማጎልበት መረጃን መሰረት አድርጎ ውሳኔ መስጠት ላይም እየተሰራበት ነው ብለዋል። በሠላም ሚኒስቴር ቅድመ ማስጠንቀቂያና የዘላቂ መፍትሄ ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ምግባሩ አያሌው  በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል ብለዋል። ተፈናቅለዋል ተብሎ ከሚገመቱት 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች መከካል ከ95 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል። የቀሩትም በራሳቸው ፍላጎትና በሌሎች ምክንያቶች መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ ተፈናቃዮቹ ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ የሚያደርግ ግጭት አለመኖሩን ተናግረዋል። ለቀሩትም ተገቢው የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። በአገር ውስጥ ተፈናቃይ ላይ ዛሬ ኢጋድ የጀመረው የምክክር መድረክ ነገ ይጠናቀቃል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም