መንግስት ከ300 በላይ እስረኞችን በይቅርታ እንዲፈቱ ወሰነ

62
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ በእስር ላይ የነበሩ 304 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲፈቱ ወሰኑ። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዛሬ እንዳስታወቀው፤ የይቅርታ ተጠቃሚዎቹ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ናቸው። እሰረኞቹ እድሜ ልክና በተለያዩ የእስር ቅጣቶች እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ነበሩ። በመንግስት የተደረገው ይቅርታ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና የፍትህ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በተደረገው ጥልቅ ተሀድሶ ውሳኔ መነሻነት መሆኑ ተጠቁሟል። በተጨማሪም ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ በይቅርታና ክስ ማቋረጥ ከማረሚያ ቤት የወጡ ታራሚዎችን አስመልክቶ የይቅርታ አሰጣጥ ሂደቱ እንደሚቀጥል በገባው ቃል መሰረት የተፈጸመ ነው። ዛሬ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት በይቅርታ የተፈቱት እስረኞቹ  ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ውግንና የሌላቸውና እስካሁን ድረስ መፈታታቸውን የማያውቁ እንደሆኑ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አመልክቷል። በይቅርታ እንዲፈቱ ከተወሰኑት መካከል 289ኙ በሽብርተኝነት ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው ናቸው። ዘጠኙ የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸው የነበሩ ሲሆን፤ ሶስቱ ደግሞ የረጅም ጊዜ ፍርድ ተወስኖባቸው በማረሚያ ቤቱ የቆዩ መሆናቸው ተመልክቷል። ሌሎች ሶስት የኬንያ ዜግነት ያላቸው ሲሆን፤ ይህም በኬንያ መንግስትና ህዝብ ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያለመና በኬንያ ታስረው የነበሩ ዜጎችን መፍታት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ነው የገለጸው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ። በዚህ ዓመት በፌዴራል ደረጃ በሽብር፣ በሙስና እና በሌሎች ልዩ ልዩ ወንጀሎች ብይን ተሰጥቶባቸውና ክሳቸው በመጣራት ሂደት ላይ የነበሩ 1 ሺ 105 ፍርደኞችና ተጠርጣሪዎች ይቅርታ ተደርጎላቸውና ክሳቸው ተቋረጦ መለቀቃቸው ይታወሳል። ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከዛሬ ጀምሮ ከተፈቱት እስረኞች መካከል የአካል ጉዳትና የጤና እክል ያለባቸው እንዳሉ ተጠቁሟል። በተመሳሳይ በክልል ያሉ እስረኞችም ከሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚፈቱም ተገልጿል። በቀጣይ መንግስት ወንጀል እንዳይፈጸም ህዝቡን በንቃት ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ተግባራት እንደሚያከናውን ነው ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ያመለከተው። ሕግ የጣሱ ግለሰቦች ላይ አስቀድሞ ማስረጃ በማሰባሰበና በቂ ማስረጃ የተገኘባቸውን በመለየት ለነጻና ገለልተኛ የዳኝነት አካል በማቅረብ ተጠያቂና ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚያደርግ አትቷል። ሕብረተሰቡ ግለሰቦቹ በፈጸሙት ወንጀል ተጸጽተው በሕግ መሰረት ይቅርታ የጠየቁና ይቅርታ የተደረገላቸው መሆኑን እንዲያውቅ ያሳሰበው ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ፤ ድጋሚ ወንጀል እንዳይፈጽሙ፣ በሰላምና በልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርገላቸው ጥሪ አቅርቧል። መንግስት በግብጽ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሪቶች በእስር ላይ የነበሩ በርካታ ዜጎችን አስፈትቶ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጉ ይታወሳል። መንግስት የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በ17 ቀናት ቆይታው በደረሰባቸው ውሳኔዎችና ባስቀመጠው አቅጣጫዎች መሰረት የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል። በተለያዩ ምክንያቶች ተከሰው በእስር ላይ የነበሩ ታራሚዎችና በክስ ሂደት ላይ የቆዩ ክሳቸው ተቋርጦ መፈታታቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም