የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል የብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት የሚያሳይ ነው - የበዓሉ ተሳታፊዎች

73
አዲስ አበባ  መስከረም  25/2012 የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል የብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት የሚያሳይ መሆኑን ከደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የመጡ ታዳሚዎች ገለጹ። ዛሬ በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዲ በተከበረው የኢሬቻ በዓል በዓል ላይ ከደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከሲዳማና ከሃላባ የመጡ እንግዶች ተሳትፈዋል። እንግዶቹ የብሔረሰባቸውን ባህላዊ ጭፈራ ለበዓሉ ታዳሚዎች አቅርበዋል። ከሃላባ የመጡት አቶ አዝማች መንታሞ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል የብሔር ብሔረሰቦችን አንድነት የሚያሳይ ነው። የኢሬቻ በዓል በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሄረሰቦች አንድነታቸውን ለማጠናከር እና የበዓሉን ደስታ ለመካፈል ጭምር እንደመጡም ገልጸዋል። ከሃላባ የመጣችው አርቲስት ዙልፋ ከማል በበኩሏ ከዚህ በፊት የተከበሩ የኢሬቻ በዓላት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔር ብሄረሰቦችን ያሳተፈ ሳይሆን የኦሮሞ ብሔር ብቻ የሚያከብረው ስለነበረ በብሔሮች መካከል አንድነት ለመፍጠር የሚያስችል እንዳልነበረ አስረድታለች። ዘንድሮ በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ በተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ ብሔር ብሄረሰቦች መታደማቸው በመካከላቸው አንድነት እንዲፈጠር አድርጓል ብላለች። የኢሬቻ በዓል ለአገራዊ ሰላምና አንድነት ያለው ፋይዳ ትልቅ በመሆኑ ሁሉም ብሔር ብሄረሰቦች በበዓሉ ላይ በመታደም አንድነትን ማጠናከር እንዳለባቸው አርቲስት ዙልፋ ገልጻለች። ከሲዳማ የመጡት አቶ ዳንጊሶ ቤሪ በበኩላቸው የሲዳማና የኦሮሞ ህዝብ አንድ በመሆኑ የኢሬቻ በዓልን በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ለማክበር እንደመጡም ተናግረዋል። ሌላው ከሲዳማ ዞን ከመጡት ታዳሚዎች ውስጥ አቶ ቦካ አንሳ እንዳሉት፤ የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ብሔር ብሄረሰቦች ነው። ከንጋቱ 11 ሰዓት ጀምሮ በተካሄደው የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓል ላይ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄ፣ ከተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የመጡ የብሔሩ አባቶች፣ እናቶች እና ወጣቶች በሆራ ሐይቅ ለአምላካቸው ምስጋና አቅርበዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም