የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም አስችሏል

147

ኢዜአ፤ መስከረም 25/2012 ኢትዮጵያ የምትከተለው  የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ  የአየር   ንብረት ለውጥ ተጽእኖን  ለመቋቋም እንዳስቻለ ተጠቆመ።

በአከባቢ፣ደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የአከባቢ ስምምነቶች ድርድር ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንሱር ደሴ እንዳሉት ኢትዮጵያ የምትከተለው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራተጂ የአየር  ንብረት  ለውጥ ተፅእኖን  ከመከላከል  አንጻር በርካታ ውጤት አስገኝቷል፡፡

ሀገሪቷ በአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ከሆኑት ሀገራት ተርታ እንደምትመደብ የገለጹት ሃላፊው፤ በተለይም ዝቅተኛ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር በመሆኑና የመልከዓ  ምድር  አቀማመጧ ለበርካታ ዓመታት  በአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖ በቀላሉ ለመጠቃት ምቹ  ሁኔታን ፈጥሯል ብለዋል ፡፡

በኢትዮጵያ 60 ከመቶ የሚሆነው ህዝብ ውሃ አጠር በሆኑ አከባቢዎች የሚኖር በመሆኑ በተደጋጋሚ በድርቅ እና ጎርፍ ሲጠቃ መቆየቱን የተናገሩት አቶ መንሱር፤ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራተጂው በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበር ከተጀመረ ወዲህ ህብረተሰቡ  ስለ  አየር  ንብረት  ለውጥ ያለው ግንዛቤ ማደጉን ጠቁመዋል።

ስትራተጂው ተግበራዊ መደረግ ከተጀመረበት 2003 ዓ.ም እስከ አሁን 20 ሚሊዮን ለሚሆን ህዝብ በአየር  ንብረት ለውጥ ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወኑም ተገልጿል።

በሁለተኛው የእድገት እና ትራንስፎርሜሽ እቅድ ዓመታት  ከግብርና እና እንስሳት ሃብት  የሚወጣው ሙቀት አማቂ የጋዝ ልቀት መቀነስ፣ ደንን ማልማት እና መጠበቅ፣ የሃይል አቅርቦት ከታዳሽ  ሃይል እንዲሆን ማድረግ  እና ቴክኖሎጂ ማስፋፋት ላይ  በትኩረት  ሲሰራ መቆየቱም ተጠቅሷል።

አብዛኛው የአገሪቱ  ህዝብ ኑሮው ከደን ጋር የተቆራኘ በመሆኑ  በደን ላይ  የሚደርሰውን  ጉዳት በመከላከል እና አዳዲስ ደኖችን በማልማት የአገሪቱ ስነ ምህዳር ለሰው ልጅ ኑሮ የተመቸ እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡

የአገሪቱ  የሃይል አቅርቦት ከታዳሽ ሃይል የሚመነጭ ነው ያሉት አቶ መንሱር፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት  ለውጥን ለመቋቋም  ታዳሽ የሃይል ምንጮችን ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚትሰራም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል በመሆንዋ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ የሚከናወኑ ድርድሮች ቀጠናውን በመወከል የበኩሏን አስተዋጽኦ ስታበረክት እንደቆየችም ነው አቶ መንሱር  የተናገሩት፡፡

ለስኬታማነቱም በአገር ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቀነስ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራተጂን  ተግባራዊ በማድረግ፤ በዓለም አቀፍ  ደረጃ ደግሞ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚደረጉ ድርድሮችን በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፈች መሆኑ ተገልጿል፡፡

 ባለፉት ሁለት ዓመታት  የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የሚወጡ ዓለም አቀፋ  ህግጋቶች እና ስምምነቶች የአገሪቱን  ፍላጎት ያማከሉ እንዲሆኑ  ተፅዕኖ ለመፍጠር ሲሰራ  እንደነበር ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት።

ኢትዮጵያ 47 አባል አገራትን ያቀፈው በዝቅተኛ የኢኮኖም ደረጃ የሚገኙ ሀገራት ጥምረት እና 48 አባል አገራት ያሉት ለአየር ንብረት ተጋላጭ አገራት ፎረም በመምራት የሀገራቱ ፍላጎት በፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት እንዲካተት አስተዋጽኦ ማበርከቷም ተጠቅሷል።

ለአየር የሙቀት መጠን  ትልቅ ድርሻ ያላቸው በኢኮኖሚ የበለጸጉ የአለም ሀገራት ተጎጂ  ለሆኑት  ካሳ እንዲከፍሉ በመሞገት ኢትዮጵያ ትታወቃለች ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሀገራቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የፋይናንስ፣ የአቅም ግንባታ እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ማድረግ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

በሁለተኛው እድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የነበሩትን ጠንካራ እና ደካማ ጎን በመገምገም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቀነስ የሚያስችል ሀገር አቀፍ የአስር ዓመት  እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ነው           አቶ መንሱር የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም