የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሠላም ተከብሯል - የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

59
አዲስ አበባ (ኢዜአ) መስከረም 24 ቀን 2012 የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ ክብረ በዓል በሠላም መከናወኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡ ላደረገው ቀና ትብብር ምስጋና አቅርቧል። በርካታ ሕዝብ የታደመበት የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሠላም እንዲከበር ከአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትና የጋር ዕቅድ በማውጣት መሰራቱን አስታውቋል። ለዕቅዱ ተፈፃሚነት በጋራ በመንቀሳቀስ ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ አብዛኛው የሰው ኃይሉንና ተሽከርካሪዎችን በወንጀል መከላከል ተግባር ላይ በማሰማራት በዓሉ በሠላም እንዲከበር መደረጉንም ገልጿል። በዓሉን ለመታደም በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከተለያዩ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ መግባቱን  በማስታወስ የበዓሉ አስተባባሪዎች ፣ ፎሌዎች፣ ታዳሚዎችና የመዲናዋ ነዋሪዎች ከፀጥታ አካላት ጋር ተባብረው በመስራታቸው ዋዜማውና የዛሬው የኢሬቻ በዓል በሠላም መጠናቀቁን አክሏል። ኮሚሽኑ ለበዓሉ በሠላም መከበር የአስተባባሪዎች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ታዳሚዎችና ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የፍተሻ ስራ ሲያከናውኑ የነበሩ ወጣቶች ላበረከቱት አስተዋፅኦ እንዲሁም ተልዕኳቸውን በላቀ ትጋት ለተወጡ መላው የፀጥታ አካላት ምስጋና አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም