ኢሬቻ የሰዎችና የተፈጥሮን መስተጋብር የማጠናከር ሚና አለው

74
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 24/2012 የኢሬቻ በዓል ከ150 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ተከብሯል። ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ በርካታ ታዳሚያን እርጥብ ቄጠማና አደይ አበባ በመያዝ ኢሬቻ ወደሚከበርበት፤ በለምለም ሳር ወደተዋበው ስፍራ ለምስጋና ተመሙ። የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻን በዓል ለማክበር ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በባህላዊ አልባሳት የደመቁ አባገዳዎች፣ ሃደ ሲንቄዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት በስፍራው ታድመዋል። ኢሬቻ ጨለማው የክረምት ወር አልፎ ብርሃን መውጣቱን በማብሰር ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፤ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለተፈጥሮም እንክብካቤ የሚደረግበት ነው። የሰው ልጆችና የተፈጥሮ መስተጋብር የበለጠ እንዲጠነክር የገዳ ስርዓት ትልቅ አስተምህሮ እንዳለው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የበዓሉ ታዳሚዎች ያወሳሉ። ይህን መስተጋብር ጠብቆ ለማቆየትና ሰው ሰራሽ የአየር ለውጥ ተጽዕኖን ለመቀነስ ተፈጥሮን መንከባከብ የአባገዳ አስተምዕሮ መሆኑን በመግለጽ። የዓለም ስጋት እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል ዛፎችን መትከልና መንከባከብ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አስተያየት ሰጪዎቹ በተለይ ኢሬቻን የመሰሉ በዓላት ሰውና ተፈጥሮን የበለጠ በማቀራረብ ረገድ ትልቅ ሚና እንዳላቸውም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የተጀመሩት የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም