ኢሬቻ የሠላምና የፍቅር በዓል መሆኑን በተግባር አይተናል - የበዓሉ ታዳሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
ኢሬቻ የሠላምና የፍቅር በዓል መሆኑን በተግባር አይተናል - የበዓሉ ታዳሚዎች
79
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 24/2012 ኢሬቻ በአንድነት የሚያሰባስብ የሠላምና የፍቅር በዓል መሆኑን 'በተግባር አይተናል' ሲሉ የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎች ተናገሩ። ከ150 ዓመት በኋላ ዛሬ በተከበረው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ፊት ላይ ደስታ ይነበባል። በመጡባቸው አካባቢዎች ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጥ የተዋቡት ታዳሚዎች ደስታቸውን በሽብሻቦ፣ በጭፈራ፣ በረገዳ እና በዜማ ገልጸዋል። እነዚህን ከተለያዩ አካባቢዎች በዓሉን ለማክበር የተገኙትና የተለያየ ብሄር ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች ኢሬቻ አቃፊ እንዲሁም የላም፣ የፍቅርና የአንድነት በዓል መሆኑን በተግባር ማየታቸውን ነው የተናገሩት። ከመኖሪያ አካባቢዎቻቸው ተነስተው በዓሉን ለመታደም ባደረጉት ጉዞ የኦሮሞ ህዝብና የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አቀባበል አድንቀዋል፤ ደስታቸውንም ገልጸዋል። መሰል ድንቅ ባህሎቻችንን በጋራ በማክበርና በማሳደግ የጋራ አገር ልንገነባ ይገባል ሲሉም ተደምጠዋል። ደስታቸውን በጭፈራ ሲገልጹ የነበሩት አባት ነስረዲን ጀማል "እኔ ሙስሊም ነኝ፤ ኢሬቻ ግን የጋራችን ነው ፈጣሪ ለዚህ አይነቱ ደስታ ስላደረሰኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው" ብለዋል። "አካል ጉዳተኝነቴ ሳያግደኝ ኢሬቻ አቅም ሆኖኝ መጥቻለሁ" ያለው ደግሞ ከአምቦ የመጣው ዋቅጅራ ነው። "ያንን ሁሉ መከራ አልፈን ዛሬ ለዚህ መድረሳችን አስደስቶኛል፤ ኢሬቻ ለሁላችን ኢሬ /ጉልበት/ ነው ሲል ገልጾታል።