አባይ በረከት እንጂ እርግማን አይደለም

113
ሰለሞን ተሰራ/ኢዜአ/ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያን የልማት ፍላጎት  በተፃረረ መንገድ የግጭት መንስኤ መሆን የለበትም።ግብፅም የውሃ ፍላጎቴ ይቀንሳል ፣የአየር ፀባይ ለውጥም ያሰጋኛል የምትለው ብሂል ጊዜ ያለፈበትና ተቀባይነት የሌለው ነው። ኢትዮጵያን፣ግብፅንና ሱዳንን የወከሉ የአካባቢ ጥበቃ ሳይንቲስቶች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተነሳ የተፈጠረው አለመግባባት በስምምነት እንዲቋጭ ያሳስባሉ። አገሮቹን በመወከል ውይይት በማድረግ ላይ የሚገኙት ተመራማሪዎች ስምምነት ላይ ለመድረስ እየመከሩ ነው። ትላንትና ዛሬ በሚያደርጉት ምክክርም በግድቡ አጠቃላይ የተፈጥሮ ተፅእኖ፣ በተለይ ደግሞ በውሃ አሞላሉ ላይ አተኩረው እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል። ግብፅ ያሳስበኛል በምትለው የውሃ አሞላል ዙሪያ ሶስቱ አገራት መስከረም 3 ቀን 2012 ዓም ደረጉት ምክክር ያለ ስምምነት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ግብፅ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በፍጥነት ተጠናቆ ወደስራ ከገባ የውሃ ኮታዬን በመቀነስ ለሰብል ምርት እጥረት ይዳርገኛል የሚል መከራከሪያ በመያዝ ስምምነቱን በሟጓተት ላይ ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት ግንባታው 68 በመቶ የደረሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል አቅርቦቱን ለማሳደግ የማይተካ ሚና ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን የማስጠበቅ ያህል እንደምትመለከተው አስታውቃለች። በዚህ ጉዳይ ግብጽ ምንም ዓይነት ተጽእኖ ማሳደር እንደማትችልም በግልፅ አቋሟን አሳይታለች። እንደ አለም ባንክ ሪፖርት 66 በመቶ የሚጠጋው የኢትዮጵያ ህዝብ የመብራት አገልግሎት አያገኝም። ይህም በዓለም ላይ መብራት ከማያገኙ አገራት ተርታ ከመጨረሻዎቹ ሶስተኛዋ አድርጓታል። ግድቡ ሲጠናቀቅ እነዚህን የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ እንደሚያደርግና አገሪቱን በኢኮኖሚ ስኬት አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚያስጉዛት ታምኖበታል። መንግስት እንደሚናገረው የግድቡ መገንባት የሰሜን አፍሪካ አገሮችን የአየር ፀባይ ለውጥ ተፅእኖ ለመከላከል ያስችላል። አሁን ላይ በናይል ሸለቆ አገራት የተከሰተው ደረቅ አየር ምክንያቱ የአየር ፀባይ ለውጥ ሲሆን የውሃ እጥረትንና ጎርፍን እንዳያስከትል ተሰግቷል። ኢትዮጵያ የያዘችው እቅድ ግን ወደ ናይል የሚፈሰውን ውሃ በማመጣጠን ችግሩን እንደሚቀርፈው የኢትዮጵያ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ ለኔቸር መፅሄት ተናግረዋል። የውሃ አሞላሉ የጊዜ ሰሌዳ ግድቡ ውሃ ተሞልቶ ስራ የሚጀምርበት ወቅት የአለመግባባቱ አንኳር ጉዳይ ነው። ግድቡ የሚይዘው ውሃ ተርባይኖቹን በማንቀሳቀስ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት መሰረት በመሆኑ በፍጥነት ተሞልቶ ወደ ስራ መግባቱ ኢትዮጵያ የማትደራደርበት ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ውሃው በአምስት ዓመት ውስጥ እንዲሞላ የምትፈልግ ሲሆን ወደ ግብጽ የሚለቀቀው ውሃ ደግሞ በአመት 35 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንዲሆን ሃሳብ አቅርባለች።ግብጽ በአስዋን ግድብ በየአመቱ በትነት የሚባክነውን ከ3 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውሃ ለማስቀረት መስራቷን ትታ ግድቡ በሰባት አመት እንዲሞላና በየአመቱ 40 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዲለቅቅላት ትፈልጋለች። ኢትዮጵያና ግብጽ መደበኛ የሆነ የውሃ ክፍፍል ስምምነት የላቸውም። እኤአ በ1959 የተፈረመው የናይል የውሃ ስምምነት ግብጽንና ሱዳንን ብቻ የያዘ ነው። በዚህም ግብፅ 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ድርሻ ስትወስድ ሱዳን በበኩሏ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዲደርሳት ተፈቅዶላታል። ስምምነቱ ግብጽ የአስዋንን ግድብ መገንባት ከጀመረች ከጥቂት ጊዜ በኋላ መፈረሙ ይታወሳል። ኢትዮጵያ የስምምነቱ አካል ባለመሆኗ ክፍፍሉን የማክበር ግዴታ የለባትም። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው መስከረም 9 ቀን 2012 ዓም ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት “የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና የአባይ ወንዝን የመጠቀም መብት የማያከብር ማንኛውም ሰምምነት ተቀባይነት የለውም።" “ኢትዮጵያ ድርድሩና ምክክሩ የሁሉንም አገሮች መብት ባማከለ ሁኔታ እንዲፈጸም ትፈልጋለች ” በማለት ኢንጅነር ስለሺ በቀለ ለኔቸር ዘጋቢ ተናግረዋል። “ ጉዳዩ ቴክኒካል በሆኑ መንገዶች ሊፈታ ይችላል ፤እኛም  ለረጅም ጊዜ አተገባበር የሚያገለግለውን ተገቢውን የስምምነት ማዕቀፍ በሳይንስና በብቁ ተሞክሮዎች በመታገዝ እናቀርባለን” ብለዋል። በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የአየር ፀባይ ለውጥ ኢንስቲቲዩት የውሃ ሃብት ተመራማሪው ኬቨን ዊለር እንደተናገሩት የሚለቀቀውን ውሃ ተከትሎ በአመታዊው አማካይ የዝናብ ምጣኔ ግብፅ በትንሹ ወይም ምንም አይነት የውሃ እጥረት አያጋጥማትም።የውሃ አሞላሉ 5 አመትም ሆነ 7 አመት ወደ ግብፅ የሚለቀቀው 35 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በቂዋ ነው። ነገር ግን ግብፅ መብቴ የምትለውን ስምምነት መሰረት በማድረግ በደረቅ ወቅት ተጨማሪ ውሃ ልትፈልግ ትችላለች ብለዋል።ነገር ግን የቅኝ ግዛት ስምምነቱ ኢትዮጵያን ባለመያዙ አገሪቱን ግዴታ ውስጥ የሚከታት ምንም አይነት ህጋዊም ሆነ ተፈጥሮአዊ ምክንያት የለም። መቀመጫቸውን ኳታር አድርገው በናይል ተፋሰስ ላይ ምርምር የሚያደረጉት ሃሪ ቬርሆቨን በሁሉም መልኩ ግብፅ ማድረግ የምትችለው ጥቂት ነገር ብቻ ነው። የካይሮ ፖሊሲ አውጪዎች ግድቡ እስኪሞላ ድረስ የሚያገኙት የውሃ መጠን ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አለባቸው በማለት አሳስበዋቸዋል። ግብፅ ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ ፍርድ ቤት ብትወስደውም ሁለቱ አገራት መስማማት ካልቻሉ ልፋቷ ከንቱ ነው። አገሮቹ መስማማት ቢችሉም እንኳን ፍርድ ቤቱ ለግብፅ ያደላል ብዬ አላስብም ብለዋል። ”ኢትዮጵያ በግዛቷ ያለውን የውሃ ሃብት ለልማት የማዋል መብት አላት” በማለት ነገሩን አስረግጠው ተናግረዋል። የግብጽ የውሃና የመስኖ ሚኒስቴር ኔቸር ላቀረበላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ አለመስጠታቸውን ዘጋቢው ጠቅሷል። ነገር ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዚህ ወር መጀመሪያ በሰጠው መግለጫ “ በኢትዮጵያ በኩል ቁርጥ ያለ የቴክኒክ ስምምነት ማድረግ አስፈላጊ ነው “በማለት ተናግረዋል። ስምምነቱ የሶስቱን አገሮች የጋራ ፍላጎት ያማካለ መሆንም አለበት ሲሉ ተደምጠዋል።ይህ የኢትዮጵያም አቋም በመሆኑ አከራካሪ አይደለም። ኢትዮጵያ ግድቡ በአጭር ጊዜ እንዲሞላ ትፈልጋለች፤ ግብፅ ደግሞ ይህንን አልቀበለም እያለች ነው ፤አዋጪው ግን ለጋራ ልማት በጋራ መነሳት ነው። አባይ በረከት አንጂ እርግማን አለመሆኑን ግብፃውያን በተለይ ደግሞ ፖለቲከኞቻቸው በመረዳት ከቅኝ ግዛት አባዜ ራሳቸውን አላቀው ለጋራ ጥቅም በጋራ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም