በደቡብ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሠላም ኮንፈረንስ ሊያካሄዱ ነው

104
    ሚዛን ሚያዝያ 29/2010 በደቡብ ክልል የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ያሳተፈ የሠላም ኮንፈረንስ ከግንቦት 1 ቀን 2010 ጀምሮ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የውጭና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መምህር ታገል ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት ለሶስት ቀናት የሚካሄደው የሰላም ኮንፍራንስ የተዘጋጀው በፌዴራል አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስቴር ፣ በደቡብ ክልል ጸጥታና አስተዳደር ቢሮና በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ትብብር ነው፡፡ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲጎለብትና ችግር ሲፈጠር መወሰድ በሚገባው መፍትሄ ላይ መምከር የኮንፈረንሱ  ዋና ዓላማው ነው፡፡ በተጨማሪም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ እርስ በርስ ልምድ የሚለዋወጡበትና በግጭት ቅድመ መከላከል ፣ በግጭት አስተዳደርና በሠላም ዕሴት ግንባታ ላይ ያተኮሩ ሰነዶች ላይም ውይይት እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2009 ዓ.ም በሀገሪቱ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በትምህርት ሚኒስትር የሠላም አምባሳደር ተሸላሚ በመሆኑ ኮንፍራንሱን የማዘጋጀት እድል እንዳገኘ ገልጸዋል፡፡ ይህም በዩኒቨርሲቲው  ያለውን ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያግዘውም ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት ያዳበረውን ስኬታማ የመማር ማስተማር ልምድና ተሞክሮ ለሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንደሚያጋራ ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ በኮንፈረንሱም በክልሉ የሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች የሚሳተፉ ሲሆን የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዝዳንቶች፣ የሠላም ፎረም አባላትና ከፌደራል የሚመለከታቸው አካላት ጨምሮ ከ500 በላይ ተሳታፊዎች መጋበዛቸው ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም