በጉጂ ዞን 8 ሺህ ሔክታር መሬት በመስኖ እየለማ ነው

69
ነገሌ ሰኔ 8/2010 በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት ከ8 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ መስኖ ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ በባለስልጣኑ የመስኖ ልማት ባለሙያዎች ቡድን መሪ አቶ ቦሩ ገልገሎ እንዳሉት በዞኑ ከመስከረም እስከ ጥር 30 የመጀመሪያው ዙር ከየካቲት አጋማሽ እስከ ነሀሴ 30 ደግሞ የሁለተኛው ዙር መስኖ ልማት የሚካሄድበት ወቅት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት በሁለተኛው ዙር የመስኖ ልማት 8 ሺህ 334 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እስካሁን 7 ሺህ 954 ሄክታር መሬት በተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘር ተሸፍኗል፡፡ እየለማ ያለው መሬት ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት በ651 ሄክታር መሬት የሚበልጥ ሲሆን ከዚሁ ልማትም 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ ከመስኖ ልማት የሚገኘውን ምርት ለማሳደግ እስካሁን 606 ኩንታል የፋብሪካና 115 ሺህ 604 ኩንታል የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ መዋሉን አብራርተዋል፡፡ በዞኑ 14 ወረዳዎች በመካሄድ ላይ ባለው ባህላዊ መስኖ ልማት በመሳተፍ ላይ ካሉት 23 ሺህ 240 አርብቶ አደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች  መካከል 5 ሺህ 370ዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ከመጀመሪያው ዙር መስኖ ልማት 3 ሚሊዮን 92 ሺህ ኩንታል የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንደተሰበሰበ ከቡድን መሪው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዞኑ ሊበን ወረዳ የኮባዲ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዱልቃድር አብዱላሂ ሁለተኛውን ዙር የመስኖ ልማት ስራ ግንቦት 4 እንደጀመሩ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በአንድ ሄክታር መሬት ላይ 150 ኪሎ ግራም የፋብሪካ ማዳበሪያ በመጠቀም ቲማቲም፣ ቃሪያና ቀይ ሽንኩርት በማልማት ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው ዙር በአንድ ሄክታር መሬት ላይ በባህላዊ መስኖ ካለሙት ቀይ ሽንኩርት 70 ኩንታል ምርት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ አልየ ሉሆም ለመስኖ ልማት ካዘጋጁት አንድ ሄክታር ተኩል መሬት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን በቀይ ሽንኩርት ዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል፡፡ በቀሪው መሬት ላይ ቲማቲም፣ ጎመንና ድንች በማልማት ከ120 ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም