በአፍሪካ የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባት ስርጭት ዝቅተኛ ነው

114
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 23/2012 በአፍሪካ የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባት ስርጭት ዝቅተኛ በመሆኑ የአህጉሪቷ መንግስታት ስርጭቱን ለማሳደግ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ተገለጸ። በአፍሪካ በቫይረሱ የክትባት ስርጭት ያሉ ምቹ አጋጣሚዎችና ፈተናዎች ላይ ትኩረቱን ያደረገው የአፍሪካ "የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ" ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ ተጀምሯል። ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ የመወያያ አጀንዳዎች፣ ቫይረሱ በአፍሪካ ያለበት ሁኔታና የክትባት ስርጭቱን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። የሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ ዋና መተላለፊያ የግብረ ስጋ ግንኙነት ሲሆን በመነካካትና በመተሻሸትም ሊተላለፍ ይችላል። በቫይረሱ የሚያዙት አብዛኞቹ ሴቶች ሲሆኑ ለማህፀን በር ጫፍ ካንሰር የመጋለጥ እድላቸውም ሰፊ ነው፤ ቫይረሱ ወንዶችን ለጉሮሮና የአፍ ውስጥ ካንሰር የሚያጋልጥ ነው። የዛምቢያ የጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከል የስራ ክፍል ረዳት ዳይሬክተር ዶክተር ሻሮን ካፓምቡዌ አፍሪካ በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስና በቫይረሱ ሳቢያ ለሚመጡ በሽታዎች ዋነኛ ተጠቂ ስትሆን ከፍተኛ ጫና መሸከሟንም ገልጸዋል። ከቫይረሱ ስርጭት አንጻር 80 በመቶ የሚሆነው የቫይረሱ ክትባት የሚያስፈልገው በአፍሪካ አህጉር ቢሆንም አሁን ያለው የክትባቱ ስርጭት 12 በመቶ ብቻ ነው። በመሆኑም የከትባቱ ስርጭት መጠን እንዲያድግ የአፍሪካ መንግስታት ፋይናንስን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ አለባቸው ብለዋል። መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የክትባት ስርጭቱ 34 በመቶ፣ በበለጸጉት አገራት ደግሞ 84 በመቶ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት በኮንጎ ብራዛቪል የአህጉራዊ ቢሮ የአዳዲስ ክትባቶች ማስተዋወቅ ኦፊሰር ዶክተር ፊዮና አቱሄቤ በአፍሪካ የክትባት ስርጭቱ እንዲስፋፋ እ.አ.አ ከ2008 እስከ 2017 ፕሮግራሞችን ቀርጾ በ27 አገራት ተግባራዊ ማድረጉን ተናግረዋል። ለሁለት ዓመት የሙከራ የክትባት ፕሮጀክት ከተካሄደ በኋላ አገራት በብሔራዊ ደረጃ የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባት መስጠት መጀመራቸውንም ገልጸዋል። በዚሁ መሰረት እ.አ.አ በ2011 ሩዋንዳ ክትባቱን በብሔራዊ ደረጃ የጀመረች የመጀመሪያዋ አገር መሆኗንና ዩጋንዳ፣ ቦትስዋናና ደቡብ አፍሪካም ሩዋንዳን ተከትለው በብሔራዊ ደረጃ መስጠት መጀመራቸውን አመልክተዋል። ኢትዮጵያም እ.አ.አ ከ2015 እስከ 2017 በትግራይና ኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች ክትባቱን በሙከራ ደረጃ መስጠቷን የተደራሽነት መጠኑም ከ90 በመቶ በላይ እንደነበር አውስተዋል። እ.አ.አ ከ2018 ጀምሮ ኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች ለሆኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሴቶች ክትባት ለመስጠት ስራዎችን መጀመሯንና ክትባት የመስጠቱን ተግባር እያከናወነች እንደሆነም ነው ዶክተር ፊዮና ያስረዱት። በአሁኑ ሰአት 14 የአፍሪካ አገራት በብሔራዊ ደረጃ ክትባቱን እየሰጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ በብሔራዊ ደረጃ ክትባቱ መሰጠት ሲጀምር በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ትምህርት ቤት ያልገቡ ሴቶች ተደራሽ አለመሆን እንዲሁም በሶማሌ ክልል የኮሌራ በሽታ መከሰቱ እንደ ፈተና የሚቆጠር እንደሆነና አሁን ችግሩን በአብዛኛው መቅረፍ እንደተቻለም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ 14 የአፍሪካ አገራት  በዓለም ዙሪያ የህጻናት ክትባትና የጤና አገልግሎት ማስፋፊያ ፕሮግራሞችን የሚረዳው ዓለም አቀፍ የለጋሾች ጥምረት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ ''ጋቪ አሊያንስ'' ፈንድ ተጠቃሚ በመሆናቸው ክትባቱን በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ ነው ብለዋል። የ"ጋቪ አሊያንስ'' ፈንድ ተጠቃሚ አገራት አንዱን ክትባት በ4 ነጥብ 5 የአሜሪካን ዶላር ሁለቱን ክትባት በ9 የአሜሪካን ዶላር ሶስቱን ክትባት በ20 የአሜሪካን ዶላር እየገዙ ለህዝቡ ተደራሽ እያደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል። የ"ጋቪ አሊያንስ'' ፈንድ ተጠቃሚ ያልሆኑ አገራት እስከ 200 የአሜሪካን ዶላር ከመድሐኒት አምራቾችና ከግል ክሊኒኮች እየገዙ እንደሚጠቀሙም ጠቅሰዋል። የክትባት ፋይናንሱ በለጋሽ አካላት ብቻ ሳይሆን መንግስታት የግሉ ዘርፍ በጋራ ለጋሽ አገራት ጋር የጋራ የፈንድ ስርአት ዘርግተው ድጋፍ ማድረግ እንዳላባቸውና በዘላቂነት መንግስታት ሙሉ የፋይናንስ ድጋፉን ማድረግ እንደሚገባቸውም ጠቅሰዋል። የክትባቱን ተደራሽነት ለማስፋት ጠንካራ የጤና ስርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ለዚህም ድርጅታቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በኬንያ የጤና ምርምር ኢንስቲትዩት የስነ ተዋልዶ የጎልማሳና የህጻናት ጤና ዋና ተመራማሪ ዶክተር ኔሊ ሙጎ እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች የክትባቱ የማዳን አቅም ከ90 በመቶ በላይ ውጤታማ ነው ብለዋል። ዛሬ በሚጠናቀቀው ጉባኤ በአፍሪካ በተለይም ከሰሀራ በታች በሚገኙ አገራት ክትባቱ ተደራሽ በማድረግ ያሉ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎች አስመልክቶ ውይይት እየተካሄደ ሲሆን ጥናትና ምርምሮችም እየቀረቡ ነው። በጉባኤው አገራት በክትባቱ ዙሪያ ያላቸውን መረጃና ልምድ እንደሚለዋወጡና መፍትሄ ሰጪ ምክረ ሀሳቦች እንደሚያቀርቡ ተገልጿል። 60 የሚደርሱ ተሳታፊዎች በታደሙበት በዚህ ጉባኤ ከአሜሪካ፣ ካናዳና ቤልጂየም የመጡ የዘርፉ ተመራማሪዎች እየተሳተፉበት ነው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም