መቱ ዩኒቨርሲቲ በሚሰጠው ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነናል - ነዋሪዎች

125
መቱ ግንቦት 8/2010 የመቱ ዩኒቨርስቲ በሚሰጣቸው የማህበረሰብ ተኮር አገልግሎት ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኙ  በኢሉአባቦር ዞን የመቱ ከተማ እና መቱ ወረዳ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  ተናገሩ፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት  ዩኒቨርስቲው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በማስተዋወቅ፣ በሙያ ስልጠና እና በትምህርት ቤቶች የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት ተጠቃሚ እያደረጋቸው ነው፡፡ በመቱ ወረዳ  አሌቡያ ቀበሌ ወጣት አርሶአደር ጥላሁን ቀነኣ እንዳለው ከሌሎች አስር ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት በተሰማሩበት የግብርና ልማት ውጤታማ እንዲሆኑ ዩኒቨርስቲው በዘመናዊ አስተራረስ፣ በምርት እንክብካቤና ግብአት አጠቃቀም በተግባር የተደገፈ ስልጠና ሰጥቷቸዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው እየተደረገለት ያለው ድጋፍ በግብርናው መስክ ያለውን እውቀት እንዳሳደገለትና  ተነሳሽነት እንደፈጠረለት አስታውቋል፡፡ ዩኒቨርስቲው በራሱ የልማት ጣቢያ በመስኖ ልማት ዙሪያ በተግባር የተደገፈ ስልጠና በመስጠትና የውሀ መሳቢያ ሞተር በማቅረብ ያደረገላቸው ድጋፍ ምርታማነታቸውን እንዳሳደገላቸው የተናገሩት ደግሞ በቡሩሳ ቀበሌ አርሶአደር ያደታ በየነ ናቸው፡፡ በዚህ አመት በመጀመሪያ ዙር መስኖ ከአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የተለያዩ የጓሮ አትክልት ሰብሎች ለገበያ በማቅረብ ከ30ሺ ብር በላይ ገቢ እንዳገኙም ተናግረዋል፡፡ የመቱ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት 10ኛ ክፍል ተማሪ የነበረችው ተማሪ ፌናን ኢሳያስ በበኩሏ በዩኒቨርስቲው መምህራን በሳምንት ሶስት ቀን  የተሰጣቸው የማጠናከሪያ ትምህርት በተለይ በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ዕውቀቷን እንዳሳደገላት ተናግራለች፡፡ የዘንድሮውን የአስረኛ ክፍል ፈተናም በአግባቡ እንደሰራችና ጥሩ ውጤት እንደምትጠብቅ ተናግራለች፡፡ የመቱ ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና ማማከር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ስማገኘው መላኩ እንዳሉት ዩኒቨርስቲው በዚህ አመት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የአካባቢውን ህብረተሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የማህበረሰብ ተኮር አገልግሎት ስራዎች አከናውኗል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በመቱና ሁሩሙ ወረዳዎች ለሚገኙ ከ150 በላይ በማህበር የተደራጁ ወጣቶች ከግብርና ስልጠና ጀምሮ እስከ ማሳ ዝግጅት ድጋፍ እና እገዛ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም የግብርና ግብአትና ምርጥ ዘር በማቅረብም ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ በአመቱ ለ192 አቅም ለሌላቸው ግለሰቦች የነጻ ህግ አገልግሎት መስጠቱንም ገልፀዋል፡፡ በመቱ ከተማ ሁለት ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ ከ600 በላይ የ10ኛ እና12ኛ ክፍል ተማሪዎች የማጠናከሪያ ትምህርት መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡ ዩኒቨርስቲው በቀጣይም በምርምር የተገኙ ውጤቶችንና ከማህበረሰቡ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ የአካባቢውን ማህበረሰብ ኑሮ እና ምርታማነት በሚያሻሽሉ የአገልግሎት መስኮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ የመቱ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት በ45 የትምህርት ክፍሎች ከ 13ሺ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ ሙያዎች በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም