ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ህጋዊና ሰላማዊ አካሄድ የሃገር ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ ነው...የሃዋሳ ከተማ አስተዳደር

68
መስከረም 23/2012 የሲዳማ ህዝብ በክልል የመደራጀት ህዝበ ውሳኔ በሃዋሳ ከተማ ህጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሔድ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎች እገዛ ወሳኝ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ገለጸ። የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ ከሐይማኖት መሪዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ትላንት ባካሔዱት የምክክር መድረክ ላይ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱት አለመረጋጋቶች በከተማዋ እድገት ላይ የራሳቸውን አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፈዋል። ከተማዋ ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ እየተመለሰች እንደሆነ ገልፀው አሁን ለተገኘው ሠላምም የሐይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ እንደሆነ አስረድተዋል ፡፡ የተገኘው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው አሁን ላይ በአባቶች ዘንድ ያለው እርቅና አንድነት በወጣቶች ዘንድም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። የሲዳማ ህዝብ በክልል ለመደራጀት ያቀረበው ጥያቄ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን የተናገሩት አቶ ጥራቱ መንግስትም ጥያቄውን ለመመለስ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ቀን መቁረጡን አውስተዋል። በሂደቱ በሲዳማ ዞንም ሆነ በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦች ድምጻቸውን የሚሰጡ እንደሆነም ጠቁመዋል። "የሲዳማ ህዝብ ብቻውን የመልማት አላማ የለውም" ያሉት ምክትል ከንቲባው ከክልል ጥያቄ ጋር አያይዘው በህዝቦች መካከል መከፋፈልን በመፍጠር የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚጥሩ ሀይሎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል። የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ህዝበ ውሳኔው በአብሮነት መንፈስ ሠላማዊና ህጋዊነቱን ጠብቆ እንዲካሄድ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። "በከተማዋ የሚገኙ ኑሯቸውን ጎዳና ላይ ያደረጉ ታዳጊዎችን ከሰብዐዊነትም አንፃር ልናያቸው" ይገባል ያሉት አቶ ጥራቱ ከሐይማኖት አባቶች ፤ የሀገር ሽማግሌዎችና ከሌሎች የህብረተሰቡ ክፍሎች ጋር በመተባበር በዘላቂነት ሕይወታቸው የሚለወጥበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰሩም አብራርተዋል። ከተሳታፊዎች መካከል የሲዳማ ዞንና የሀዋሳ ከተማ ሸሪአ ፍርድ ቤት ዳኛና የደቡብ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ ሀጂ ቃሲም አደም ሠላምን ማስፈን የፀጥታ አካላት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል። ሁላችንም የሠላም ባለቤቶች ነን ያሉት ሀጂ ቃሲም ትናንሽ አለመግባባቶች ገዝፈው የከፉ ችግሮች ከመፈጠራቸው አስቀድሞ በየአካባቢው ያሉ የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ፈጥነው ሊያስቆሙ እንደሚገባ አመልክተዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት የቦርድ ሰብሳቢ ፓስተር ጌቱ አያሌው እንደገለጹት ከዚህ በፊት በከተማዋ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሲዳማና ወላይታ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን መቃቃር ለመፍታት እርቅ የማውረድ ሥራ ሲሰሩ ቆይተዋል። በሐምሌ 11/2011 እንደዚሁ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለማብረድና ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ከሀይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል። ችግሩን የፈጠረው የሲዳማ ህዝብ ሳይሆን ጥቂት አክራሪ አክቲቪስቶችና ግለሰቦች መሆናቸውን ገልፀው "በህዝቡ ገፅታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደሩ ይህንን ገፅታ ለመቀየር መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል። በከተማዋ ውስጥ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ የተለያዩ አሉባልታዎች እንደሚወሩ የተናገሩት በሀዋሳ ከተማ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት ባሻ ጋቢሳ ሙለታ በበኩላቸው "ይህንን ማስቀረትና ልጆቻችንን መምከር ይጠበቅብናል" ብለዋል። በምክክር መድረኩ ላይ በሃዋሳ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ የተያዩ የሃይማኖት አባቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም