እየሰፋ የመጣውን የፖለቲካ ምህዳር ለመጠቀም...

242
በቁምልኝ አያሌው (ኢዜአ)  ሃገራችን ከንጉሠ ነገሥት ወይም ከአፄዎቹ የፊውዳሊዝም ሥርዓት፣ እራሱን ሶሻሊስት ብሎ ከሚጠራው ወታደራዊው መንግሥት እስከ አሁኑ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በተለያየ ርዕዮተ-ዓለምና በተለያዩ መሪዎቿ ስትተዳደርና ስትመራ ቆይታለች፡፡ በነዚህ የአስተዳደር ስርዓቶች ውስጥም ሃገሪቷ በርካታ አዎንታዊና አሉታዊ ሁነቶችን ስታስተናግድ ቆይታለች። ባለፉት ሶስት አስርተ አመታት ውስጥም የዜጎች በነፃነት የፖለቲካ ተወካዮቻቸውን የመምረጥ መብትም ህልም ሆኖ ቆይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ ግን ፖለቲካው በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ የለውጥ ተስፋን ለያሳይ ችሏል። የፖለቲካ ምህዳሩም ወትሮ ከነበረው የሰፋና በርካታ ዕድሎችን የሚሰጥ ሆኗል። ውዷ ሃገራችንን በአሉታዊነት ከፈተኗት ዓበይት ጉዳዮች ስንነሳ በ1966 ዓ/ም በወሎና ትግራይ የተከሰተው አሰቃቂ ችጋር /ርሃብ/ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቿ ማለቃቸውና መፈናቀላቸው ለህዝባዊ አብዮትና እንቅስቃሴ እንደመነሻ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡ በመቀጠልም የዚችውን ሃገር ህዝቦች ለዘመናት ወደ ኋላ ከጎተቷት ፖለቲካዊ ጉዳዩች መካከልም ቂም፣ በቀል፣ የደቦ ፍርድ፣ የሃይል አደረጃጀት ብሎም የደፍጥጠህ ግዛ የጭቆና ቀንበር ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳም ‹‹ የሚደራጁ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም ስብሰብ ሳይሆኑ ብሶት፤ ቂም በቀልና ምሬት የወለዳቸው ፓርቲዎች እንዲኖሩ ማድረጉን›› በሃገሪቱ ፖለቲካ ለዓመታት የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉት በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ መምህር፣ ምሁርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው፡፡ ከዚያኔው 1960ዎቹ ጀምሮ የሃገራችን ዜጎች ዲሞክራሲዊ ስርዓትን ለመገንባት በተደገረ ትግል የመድብለ-ፓርቲ ስርዓት ስላልዳበረና ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ስላልተፈጠረ የራሱ የሆነ አሉታዊ ጫና አሳድሮ ቆይቷል፡፡ በእርስ በእርስ ጦርነት፣ በመጠላለፍ፣ በሴራ ፖለቲካና በተለያዩ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎች የተፈተነችው ታላቅ ሃገር ከበርካታ ውጣ ውረዶችና መሰናክሎች በኋላ ይኸው እዚህ ደርሳለች፡፡ በዚህ ሂደትም ድል ለዲሞክራሲ፣ ዲሞክራሲ አሁኑኑ፣ ፍትህ ለሁሉም የሚሉት የዜጎች ጥሪና መፈክር እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ቢሆን እየተስተጋባ መቆየቱን ለመረዳት የቅርብ ነጋሪ አያሻንም፡፡ አለመግባባትና በሃሳብ የበላይነት አለማመን ደግሞ ለአንድ ሃገር ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓትን ለመገንባት ትልቁ በሽታ ነው፡፡ አሁን ግን ሁኔታዎች ሁሉ መልካም አጋጣሚ በሚባል የለውጥ መንገድ የምትገኘውን ሃገራችን በጋራ ሆነን ወደ ተሻለ ዲሞክራሲያዊ  ማማ ማሻገር ከኛ ከዜጎቿ ይጠበቃልና  መልካም የሆነች ሃገራችንን መፍጠር የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድርሻ ነው፡፡ የመጣውን ለውጥ ወደተሻለ ከፍታ እንዲደርስ ከታሰበ ‹‹የምሁራንና የተለያዩ አካላትን ተሳትፎ በመጠቆም ለመለወጥ እየሄድን ካለንበት መንገድ በተቃራኒ የቆሙ ሃይሎች መድረክ ላይ በመቅረብ የማሸነፍና የመሸነፍ ልምድ መዳበር አለበት›› ይላሉ ፖለቲከኛው አቶ ሙሼ ሰሙ። የዚያኔው የ60ዎቹ ጥሪ ከነበሩት “ስራ ለስራ አጦችን” የሚለው መፈክር አሁንም ውዷ ምድራችን ኢትዮዮጵያ እየፈተኗት ካሉ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ የስራ አጥነት ውጤቱ ደግሞ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶቻችን ከከተማ እስከ ገጠሪቷ የሃገራችን ክፍል ድረስ ለአሰቃቂ ስደትና ችግር ከማጋለጥም አለፍ ብሎ ለተለያዩ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት ባሪያና ተገዥ እስረኛ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ፍትህ ሲጓደል፣ ፖለቲካዊ አስተዳደር ስርዓት ብልሽት ሲገጥመው፣ ብዛህነትን ማስተናገድ ሲያቅተንና የዲሞክራሲያዊ ግንባታ ሂደታችን አዘቅጥ ውስጥ ሲገባ መሆኑን ይገነዘቧል፡፡ ከታሪክ እደምንረዳውም ሃገራችን ኢትዮጵያን ለበርካታ ጊዜያት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተቋዳሽ ትሆን ዘንድ  የዲሞክራሲ ጎህ ፈገግ አሰኝቷት /አጓጉቷት/  አልፏል፡፡ ይህ እንዳይሆን ከታሰበና ዘላቂነት ያለው ዲሞክራሲዊ የፖለቲካ ስርዓት ለመገንባት ከተፈለገ ‹‹አሁን ላይ ሃገሪቱ መንታ መንገድ ላይ እንድትሆን መሰረታዊ ምክኒያቱ መንግስት ህግና ስርዓትን በአግባቡ ማስከበር አለመቻሉ ነው›› ያሉት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀመንበሩ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ ሲሆኑ ‹‹ማንኛውም አይነት ተቃውሞም ሆነ የሀሳብ ልዩነት በሰለጠነ መንገድ መካሄድ ይኖርበታል›› ይላሉ። ይህንኑ ሃሳብ በማጠናከርም የአረና ፓርቲ ሊቀ-መንበር የሆኑት አቶ አብርሃ ደስታ ‹‹ያለሰላም የፖለቲካ እንቅስቃሴም ሆነ ህዝብ እና ሀገር አይኖሩምና ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ያለምንም ልዩነት ቅድሚያ ለሰላም ስሩ›› ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ ባሳለፍነው ዓመት ምንም እንኳን በርካታ ውጣ ውረድ ያሳለፍን ዜጎች ብንሆንም  ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የፖለቲካ ተንታኞች በኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር መከበር፣ በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ፣ በሕግ የበላይነት መረጋገጥ፣ በሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በብሔረሰቦች እኩልነት፣ አንድነቷን በማጎለበተ ያለች ኢትዮጵያ ለማየት የሚደረገውን ጥረት ያደንቃሉ፡፡ ስለሆነም የነበሩ እንከኖችን በመቅረፍ፣ በማሻሻልና መልካም እሳቤዎችን በማስቀጠል ብሎም ከልብ የመለወጥ መርህን በመላበስ ለህዝቦቿ የተሻለች ኢትዮጵያን በተሻለ መንገድ ማስኬድና መምራት ግድ የሚልበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ምክኒያቱም ለሰው ልጆች ሁለንተናዊ አብሮነት፣ እድገትና ብልፅግና የተሻለ ለውጥና ምቹ የአስተዳደር ስርዓት መዘርጋት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ በተለይም ለዛሬዋ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ መስተጋብሮችን ቃኝቶ ያሳለፍነውን ሂደት በመዳሰስ አሁናዊነታችን ልናይ የቻልነው በለውጥና በመለወጥ ሃይል ነው፡፡ ‹‹እየተካሄደ ያለው ለውጥ መጀመሪያም ህገ መንግሥቱ ላይ የነበሩና በረጅም ሂደት በመመሪያ፣ በደንብ፣ በፖሊሲ አንዳንዴም በጉልበትና በውሳኔ እየተጨፈለቁና እየተደመሰሱ የመጡ መሆናቸውን›› ፖለቲከኛና የፓርቲ አመራሩ አቶ ሙሼ ሰሙ ይናገራል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን የስራ እንቅስቃሴ በሚመለከት ‹‹ህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ያለ ፍርድ ቤት መታሰርና ያለ ጠያቂ መቅረት፣ መገረፍና አካል መጉደል የመሳሰሉት ህገ መንግስቱ የማይደግፋቸው ድርጊቶችና ሃሳቦች እንዲቀለበሱ ነው ያደረገውም›› ይላል። እንደማሳያ እንኳን የኢፌዴሪ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በማሰብ በርካታ የማሻሸያ እርምጃዎችን ሲወስዱ ይሰተዋላል፡፡ ለውጡን በሚመለከት ‹‹በዚህ የፖለቲካ ምህዳር የማስፋት ጉዞ የወጣቶች፣ ሴቶች፣ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች መብት ማስከበር፣ ግጭቶችን መፍታት፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በተያያዘ የተቀመጡ ድንጋጌዎች ይሻሻላሉ ብለን እናስባለን›› ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡት ደግሞ በክርስቲያን በጎ አድራጎት ድርጅቶች፣ ማህበራትና ህብረት ዋና ዳይሬክተሩ መሸሻ ሸዋረጋ (ዶ/ር) ናቸው። ከነዚህ የለውጥና የማሻሻያ መርሃ-ግብሮች መካከልም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና የሚዲያ አካላትንም ጨምሮ ያለው የፖለቲካ መጫዎቻ ሜዳ አልመችልህ ሲላቸው ለመሰደድ ተገደው ኖሯቸውን በሃገረ ኤርትራ፣ አሜሪካና አውሮፓ አድርገው ለመንቀሳቀስ ተገደው ነበር፡፡  በአሁኑ ወቅት ግን የሃገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ኢትዮጵያ በለውጥ ጎዳና ላይ ነች፡፡ የፖለቲካ እስረኞች፣ ጦማሪያን፣ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ-መብት ተማጋቾች ከነበሩበት አስቃቂ የማጎሪያ ቤትም ወጥተው በነፃነት የቀድሞ ስራዎቻቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንን የለውጥ ጉዳና አስመልክቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አስናቀ ከፍአለ (ዶ/ር) ‹‹መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋቱ እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አገር ውስጥ እንዲገቡ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ በጎ ጅማሮ ነው›› ሲሉ ይናገራሉ :: በዚህም እነዚሁ ኑሯቸውን ከሃገር ውጪ በማድረግ በሃይል መንግስት ለመመስረት ዓላማ አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች ወደ ሃገራቸው ተመልሰው ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አክብረው ለመስራት ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ተመቻችቶላቸዋል፡፡ የለውጡ ተቋዳሽ የሆናቹህ ፖለቲከኞች፣ ጦማሪያን፣ ጋዜጠኞችና የሚዲያ አካላት ሆይ ሃላፊነት በተሞላበት መልኩ ለሃገረ አንድነት የሚበጁ ሃገራችንና ህዝቦቿን የሚያቀራርቡ ጉዳዩችን በመስራት የለውጡ ታሪክ ሰሪ አንድ አካል መሆን ያስፈልጋል፡፡ ይኸው ለውጥ ከመጣ ወዲህ ሃገር ውስጥ ያሉና ሯቸውን ውጪ አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ ጋር በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል፡፡ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴም እንዲሁ ለውጡንና የለውጡን ሂደት በሚመለከት ሰኔ 10/2011 ዓ/ም ባካሄደው መደበኛ ስብስባ በሀገራችን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ በመወያየት በቀጣይ ስለሚወሰዱ እርምጃዎችና አቅጣጫዎችን ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡ በዚህም ‹‹በፖለቲካው መስክ በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም በሀገራችን የፀጥታ መደፍረስ፣ በአመራር ቁርጠኝነት ማነስ፣ የጋዜጠኝነት ወይም አክቲቪስትነትና ፖለቲከኝነት መምታት፣ የሀገረ-መንግስት፤ የብሔር መንግስትና፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረታዊ ጥያቄዎች አፍጥጠው የመጡና አፋጣኝ መፍትሔ የሚሹ መሆኑን የጠቆመው ኮሚቴው ይህ ሂደት ደግሞ ለመድብለ-ፓርቲ ስርዓት ግንባታችን ትልቅ ተግዳሮት እየሆነ መምጣቱን›› ጠቁሟል፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ የሚዲያ አካላትና አክቲቪስቶች በአስተሳሰብ ደረጃቸው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ምንነትን በሚገባ የሚረዱ ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡ ስለሆነም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶች ይህንኑ ሰፊ የለውጥ ምህዳር በሚገባ በመጠቀም ሃገራቸን ኢትዮጵንና ህዝቦቿን የሚጠቅሙ ጉዳዮች በመከወን ሃላፊነት በተሞላበት መንፈስ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም ከአሁን በፊት ተዘግተው የነበሩ እስከ 246 የሚደርሱ ድረ-ገፆችና የማህበራዊ መገናኛ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ ተደርጎ ሃሳባቸውን በነፃነት እንዲያንሸራሽሩ በመደረጉ የተጀመረውን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የማጎልበት ጥረት በተጠናከረ መንገድ ለማስቀጠል በር ከፋች አድርጎታል፡፡ ይህንን የዲሞክራሲዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ደግሞ እነዚሁ አካላት ጉልህ ድርሻ ስላላቸው የሃገራቸውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት መንቀሳቀስ ይገባቸዋል፡፡ የሃገራችን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረ፣ እየሰፋና አስቻይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩም ይገኛል፡፡ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ባህል ያለ ሃሳብ ብዝሃነት፣ ትብብር፣ መቻቻልና መከባበር በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ይቆጠራልና ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ገንቢና አቃፊ ሚናቸውን መጫወት የሚችሉበት ወቅትም አሁን ነው፡፡ ይህ ሲሆን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደታችን ስር ሰዶ የሚፈለገውን ርቀት ከተጓዘ ሃገራችን ኢትዮጵያ ለዜጎቿ ምቹ ምድር የማድረጉ ውጥን ሩቅ አይሆንም፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞቻችን ለሰላማዊ ትግል ቁርጠኛ የሆነ አቋም በመያዝ እራሳቸውን አዘጋጅተው መንቅሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የኢፌዴሪ መንግስት የዲሞክራሲ ስርዓት ሂደቱን ለመገንባት የሚወሰዱ የፖለቲካ ምህዳር ማሻሸያ እርምጃዎችን አይቶ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይህም መሆኑ ደግሞ ሃገራችን ውስጥ ማንኛውንም ዓይነት የፖለቲካ ምልከታና ህዝቡን እወክላለሁ ያለ አካል ሃሳቡን እንደልቡ እንዲገልፅና እየሰፋ በመጣው የፖለቲካ ምህዳር የራሱን አስተዋፆ እንዲበረክት አስችሎታል፡፡ በተደማሪነት ደግሞ ይህንኑ ምቹ የፖለቲካ ምህዳር በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ በማዋል ለሃገሪቷና ህዝቦቿ ይበል በሚያሰኝ መንገድ መጓዝ በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጓቸው እያንዳንዷ እንቅስቃሴ በሃገራችን የተጀመረውን እጅግ ተስፋ ሰጪ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የፖለቲካ ምህዳሩን መስፋት የሚያጎለብተውም ጭምር ስለሆነ ነው። መንግስትም ይህንኑ የፖለቲካ ምህዳር እንዲጎለብትና እንዲሰፋ እያደረገ ያለው ጥረት ህዝቦች የሃገራቸው ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውን በማመን የሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ስለሚገነዘብም እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመሆኑም አገራችን ውስጥ ያሉ ሁሉም ዓይነት አስተሳሰቦች  ለህዝብና ሃገር በሚጠቅም መልኩ  እየሰፋ ባለው የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና አካታች  በሆነው የፖለቲካ  ምህዳር ውስጥ እንዲንፀባረቁ ይፈልጋል። የሁሉም የአገራችን ህብረ-ብሄረሰቦች ጥያቄና ድምፅ እንዲሰማ ምላሽም እንዲያገኝ በሃገራችን ውስጥ ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተገቢው መንገድ  ተደራጅተውና ታንፀው  የሚወክሉትን ህዝብ ፍላጎት ማንፀባረቅ ይጠበቅባቸዋል። በአዲሲቷ የተስፋ አድማስ ኢትዮጵያ ህዝቦቿ እንዲያስተዳድሯት የሚፈልጓትን ይመርጣሉ እንጂ እንዳሳለፈችው የኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድና  አሰራር ሊዘጋ ከፊት ለፊታችን ተቃርቧልና በተገቢው መንገድ ማስተናገድ ግድ ይለናል። ይህንን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ህብረ-ብሄራዊነትን የተላበሰ ሃገረ ግንባታችን በፅኑ አለት ላይ ለመመስረት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብሎም የሚመለከታቸው አካላት አቋም ይዘው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተለይም አሁን ጊዜው የይቅርታ፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የሰላም እና የዲሞክራሲ በሆነበት ሰዓት ለምን እንደዚህ ዓይነት አመለካከትና ሃሳብ አንፀባረክ ተብሎ የሚፈረጅበት፣ የሚታሰርበትና የሚሳደድበት ያ ዘመን ይህ እንዳይሆን ተባብሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ሃገርንና ህዝብን አገለግላለሁ ብለው የተሰለፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህን በመስፋት ላይ የሚገኝ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደትና የፖለቲካ ምህዳር ጠቃሚ የሆኑ አጀንዳዎችን ይዞ በኃላፊነት መንፈስ መገልገል ይጠይቃል። ሃገራችን ውስጥ ልማትንም ይሁን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደትን ለማሳለጥ የሚከናወኑ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴዎች ማንንም ለማስደሰት አሊያም ለማስከፋት ሳይሆን ሃገራችን ኢትዮጵያ ለውጥ አስፈልጓት አንገቷን ደፍታ ስታዝን ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው የታገሉና የተሰው ህዝቦቿን በተለይም ደግሞ ወጣቶቿን በፅኑ መሰረት ላይ የቆመችን ሃገር አስረክቦ ለማስቀጠል የታለመ ነው፡፡ የኢፌዲሪን መንግሰት ለማስተዳደር ስልጣን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም (ዶ/ር) የሚያከናውኗቸው መልካም እሳቤዎች  ለሃገርና ህዝብ ጥቅም ሲባል መሆኑን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በተለያዩ ርዕዮተ-ዓለም የተደራጁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምህዳሩ መጎልበት የሚጠበቅባቸውን ሃገራዊ ድርሻ መወጣት ግድ ይላቸዋል። ከሁሉም በፊት ግን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ሳይሸማቀቁ፣ ሳይፈሩና የሌሎችን ስብዕና ብሎም ተፈጥሯዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ጠብቀው  በእኩልነትና በነፃነት የሚንቀሳቀሱባት ኢትዮጵያን መፍጠር የሁሉም ዜጋ ድርሻ  መሆን ይኖርበታል። አሁን በሃገሪቱ ውስጥ ያለው ያልተረጋጋ የፖለቲካ አየር የተረጋጋና ስረ-መሬት የያዘ እንዲሆን ተባብሮና ተደጋግፎ መሰራት ይጠይቃል፡፡ በመንግስትና ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ በኩል ፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ጀምሮ እስከ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ማድረጉ እንደተጠበቀ ሆኖ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናም የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳልና...፡፡ በግልፅነት፣ ተጠያቂነትና በሃላፊነት መንፈስ በመንቀሳቀስ አባላቶቻቸው የተጀመረውን ዲሞክራሲያዊ ግንባታ ሂደት መርህ አድርገው ብቻ እንዲሰሩ በማድረግ ሃገርና ህዝብ የሚፈልገውን ተግባር ማከናወን ለሁላችንም ይጠቅማል፡፡ ይህን የተጀመረውን ሰፊ የፖለቲካ ምህዳር ተከትሎ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንክረውና ወደ ተሻለ የትግል ምዕራፍ ለመሸጋገር የሚያስችላቸውን አንድነት በመፍጠር ተሰባስበው ራዕይና ፕሮግራሞቻቸውን ለህዝብ የሚያቀርቡበት መድረክ እየተፈጠረ መሆኑ ከለውጡ ድል ማግስት የተጎናፀፉት አዎንታዊ ሁናቴ መሆኑ በመልካም ይነሳላቸዋል፡፡ ይኸኛው ተግባራቸው የሚበጅና ምስጋና የሚቸረው ሲሆን ከዚህ በተደማሪነትም ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራርቡ ተግባራዊ  እንቅስቃሴዎችን ማድረግ፣  ለህግ-የበላይነት መከበር ተባብሮ መስራት፣ ባለመጠላለፍና ለሃገራዊ አንድነት የሚደረገውን ጥረት ማሳለጥም  ይገባል፡፡ የሃገራችን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅድሚያ ብሔራዊ ወይም ሃገራዊ ሁኔታዎችን ግንዛቤ ውስጥ አስገብተው የጋራ ስትራቴጂካዊ ጥቅሞች ላይ በመመስረት አማራጮቻቸውን እንደ ፖለቲካዊ ቤተሰብ እያቀረቡ በሰላማዊ መንገዶች የሚፎካከሩበት እድሉ ቀርቦላቹሃልና በሚገባ መጠቀሙ ይበጃል፡፡ ይህ የተጀመረው የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት ሃገራችን ኢትዮጵያን በታሪክ ውስጥ ፈገግ አሰኝተዋት ሳትጠቀምባቸው ካለፉት አንዱ ነውና የኢትዮጵያ ገዥውና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአዲሲቷን የተስፋ አድማስና ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መሃንዲሶች ይሆኑ ዘንድ መጋበዝዎን ልብ ይበሉ ልብ ያለው ያስተውላል መልካም መልካሙንም ያደርጋልና፡፡ ቸር እንሰንብት!!  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም