በደብረብርሃን ከተማ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ በወቅቱ ስለማይነሳ ለጤና ችግር ተዳርገናል - ነዋሪዎች

74
ደብረ ብርሃን  ሰኔ 8/2010 በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የሚፈጠረውን ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ በወቅቱ ማንሳት ባለመቻሉ በጤናችን ላይ ተጽኖ ፈጥሮብናል ሲሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለፁ። የ06 ቀበሌ ነዋሪ አቶ በሱፍቃድ ነባሩ “በከተማው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ በአግባቡ ስለማይወገድ በጤናችን ላይ ችግር እየተፈጠረ ነው'' ብለዋል። ሆቴሎችና ስጋ ቤቶች ያለማንም ከልካይ በየቦታው የሚጥሉት ቆሻሻ የከተማውን ውበት ከማበላሸቱም በላይ የነዋሪዎችን የእለት ተእለት ኑሮ እያስተጓጎለ ነው፡፡ በቆሻሻው በሚፈጠረው ሽታም ለመተንፈሻ አካል በሽታ መጋለጣቸውንና ልጆቻቸውም እንደልባቸው ለመንቀሳቀስም ሆነ በአካባቢያቸው ለመጫወት መቸገራቸውን ገልፀዋል፡፡ የ02 ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ እታበዝ ሐጅ በ06ና 02 ቀበሌ መካከል በርካታ ቆሻሻ ስለሚጣል ወጥተን ለመግባት ተቸግረናል ። “በአንድ ኩንታል ደረቅ ቆሻሻ 15 ብር እየከፈልን ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እንዲሄድ ብናደርግም በቅንጅት ማነስና በጨለማ በየአካባቢው ስለሚጣል ከብክለት አልዳንም'' ብለዋል፡፡ የተዘጋጁ አሮጌ የቆሻሻ ገንዳዎችም ሲሞሉ ተቆጣጥሮ የሚያስወግድ ባለመኖሩ አካባቢውን እየበከለ ነው ያሉት ደግሞ የ09 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ብርሃኑ ይመር ናቸው፡፡ በተለይ በቂ የማፋሰሻ ቦይ ባለመኖሩ ጎርፉ ወደ መንገድ በመፍስስ ውሀ የሚያቁሩ ቦታዎችን በመፍጠሩ  በውስጣቸው በተጠራቀመው ፕላስቲክ፣ ሀይላንድ፣ አሮጌ አልባሳትና የጠርሙስ ስብርባሪዎች እንደልብ ለመንቀሳቀስ አዳጋች እንደሆነባቸው  ገልፀዋል፡፡ በደብረብርሃን ከተማ የከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን አገልግሎት ጽህፈት ቤት የከተማ ፕላን አፈጻጸም ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪ ተወካይ አቶ ደምሰው ግባይ በበኩላቸው ችግሩን ለመቅረፍ ባለድርሻ አካለትን ባሳተፈ መንገድ ለመስራት ቢሞከርም ለውጥ አልመጣም። በተለይም በበጀት እጥረት ምክንያት በየቤቱ የሚመነጭ ቆሻሻን የሚያስወግድ አካል ባለመኖሩ መፍትሄ መስጠት አልተቻለም፡፡ “ህብረተሰቡ በክፍያ እንዲያስወግድ ቢደረግም አቅም የሌለው ጨለማን ተገን አድርጎ በየቦታው ስለሚጥል መቆጣጠር ባለመቻሉ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል'' ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለማቃለል ነባር ቆሻሻ ማስወገጃ ቦታዎች በሽቦ ታጥረውና ዘበኛ ተቀጥሮላቸው በተወሰነ መፍትሄ ለመስጠት ተሞክሯል። ቀጣይ በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጅ በ07 የገጠር ቀበሌ 9 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ ዘመናዊ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ ለመስራት ታቅዷ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የደብረብርሃን ከተማ መጠጥ ዉሃ ፈሳሽ አገልግሎት ምክትል ስራ አስኬያጅ አቶ ምዕራፍ አብይ በበኩላቸው ያሏቸዉን ሁለት ቦቴዎች ተጠቅመው ፈሳሽ ቆሻሻዎችን ከከተማው ወጣ ብሎ በተዘጋጀው ጊዜያዊ ቦታ ማስወገድ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ “በጊዜያዊነት የተመረጠው ቦታ ተስተካክሎ ከአንድ ወር በኋላ ሙሉ በሙሉ መጠቀም ስንጀምር ችግሩ ይቃለላል'' ያሉት አቶ ምእራፍ  እስከዚያው ድረስ ህብረተሰቡ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎችን በአግባቡ በማስወገድ  የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮች በቆሻሻ እንዳይደፈኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ ውሃ የሚያቁሩ ቦታዎችንም እንዲፋሰሱ እየተደረገ ሲሆን ከሁለት በላይ ቆሻሻ አስወጋጅ ኢንተርፕራይዞች ተደራጅተረው ስራ መጀመራቸውንም አስታውቀዋል። ባለፉት ወራትም 4 ሺህ 710 ሜትር ኩብ ደረቅ ቆሻሻ መወገዱንና ይህም በከተማው ካለዉ ደረቅ ቆሻሻ 60 በመቶውን ብቻ እንደሚሸፍን ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም