የመንግስታቱ ድርጅት በኬንያ ሁለት መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየሰራ ነው

65
አዲስ አበባ ኢዜአ መስከረም 22/2012 የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት በኬንያ በካኩማ እና ዳዳብ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። ድርጅቱ በኬንያ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር በመነጋገር በካኩማ እና ዳዳብ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል። በመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች መርጃ ድርጅት የኬንያ ኃላፊ ፈትያ አብደላ እንደገለጹት ከመጠለያ ጣቢያዎቹ መመለስ የሚፈልጉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን አሉ። በመሆኑም እነዚህን ወገኖች ለመመለስ ድርጅቱ በናይሮቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር ተባብሮ የመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል። በኬንያ የኢፌዲሪ አምባሳደር መለስ ዓለም በበኩላቸው መንግስት ለዜጎች ደህንነት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎ በተለያዩ ሀገራት በስደት ላይ የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እየተመለሱ መሆኑንም ገልጸዋል። አምባሳደር መለስ ከፈቲያ አብደላ ጋር ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ከጎረቤት አገሮች የተፈናቀሉ ስደተኞችን አስጠልላ እንደምትገኝ ገልጸውላቸዋል። ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር በቅርበት በመስራት የስደተኞች ደህንነት እንዲጠበቅ እንደምትሰራ መግለፃቸውን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም