በምእራብ ሸዋ ዞን 46 ሺህ ሔክታር መሬት በቅባት እህል የመሸፈን ስራ እየተከናወነ ነው

2098

አምቦ ሰኔ 8/2010 በምዕራብ ሸዋ ዞን በዘንድሮው መኸር እርሻ ከ46 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቅባት እህል ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በጽህፈት ቤቱ የአዝርዕት ልማት ባለሙያ  አቶ ደጉ ረጋሳ እንዳስታወቁት በዞኑ በተያዘው የመኸር ወቅት ኑግ፣ ተልባ፣ ሰሊጥ፣ ጎመንዘርና ለውዝ ለማልማት የእርሻና የዘር ስራ እየተከናወነ ነው፡፡

ካለፈው ወር ወዲህ በተካሄደው እንቅስቃሴ 3 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን እስከ ነሐሴ አጋማሽ ድረስ የዘር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ባለሙያው እንዳሉት ዘንድሮ በቅባት እህል ለመሸፈን የታቀደው መሬት ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ7 በመቶ ብልጫ አለው።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲቻል ከግብርና ምርምር ማዕከላት የተለቀቁ የተሻሻሉ የቅባት እህል ዝርያዎች  ለአርሶ አደሩ ቀደም ብሎ መሰራጨቱን ጠቁመዋል።

በአጠቃላይ ከሚለማው መሬት ከ504 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ ግንደበረት ወረዳ ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ጫልቺሳ ነገዎ  በሰጡት አስተያየት ከምግብ ሰብል በተጓዳኝ በገበያ አዋጪ የሆነ  የቅባት እህል በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።

በተለይ ሰሊጥ በገበያው ላይ አዋጪ በመሆኑ ዘንድሮ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ለማልማት እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአምቦ ወረዳ አርሶ አደር መገርሳ ቶልቻ በበኩላቸው በመኸር እርሻው በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ ተልባ መዝራታቸውን ገልጸው ከዚህም ስድስት ኩንታል ምርት ይጠብቃሉ።

እየጣለ ያለውን ዝናብ በመጠቀም የዘሩት ተልባና ኑግ  በተሻለ ቁመና ላይ እንደሚገኝና ጥሩ ምርት አገኛለሁ ብለው እንደሚጠብቁ የተናገሩት ደግሞ የሊበን ጃዊ ወረዳ አርሶ አደር ቶለሳ ፊጣ ናቸው፡፡