በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው ክረምት ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት ይኖራል - ብሄራዊ ሚትዎሮሎጂ

102
ጋምቤላ ሰኔ 8/2010 በጋምቤላ ክልል በዘንድሮው የክረምት ወራት በሚጥለው ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የብሄራዊ ሚትዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስጠነቀቀ። የክልሉ አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በበኩሉ የሜትሮዎሎጂ ትንቢያን መሰረት በማድረግ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጿል። በኤጀንሲው የጋምቤላ ክልል የሚትዎሮሎጂ  አገልግሎት ማዕከል ዳሬክትር አቶ በቃሉ ተማነ ለኢዜአ እንደገለጹት ከመጪው ሐምሌ ወር ጀምሮ በክልሉና አካባቢው በሚጥለው ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የአየር ትንበያ መረጃ ያመለክታል ። የዘንደሮው ክረምት የዝናብ ስርጭት በ1996 ዓ.ም ከነበረው ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት መጠን ጋር ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በክልሉ አብዛኛው ምዕራባዊ አካባቢ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ተናግረዋል። በተለይም የክልሉ መልካአምድራዊ አቀማመጥ ዝቅተኛ በመሆኑና ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች በሚጥለው ከፍተኛ ዝናብ ባሮን ጭምሮ ክልሉን የሚያቋርጡ ወንዞች ሞልትው በመፍሰስ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችል ገልጸዋል። ከሚከሰተው የጎርፍ አደጋ ችግር ጋር ተያይዞም የወባ በሽታ ስርጭት ሊጨምር የሚችልበትና የውሃ ወለድ በሽታዎች ክስተት ሊፈጠር እንደሚችልም ጠቁመዋል። ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ማዕከሉ የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የአየር ትንበያ መረጃዎች እንደየተቋማቱ ፍላጎት ተደራሽ የማድረግ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በክልሉ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስተና ኤጀንሲ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስተባበሪ አቶ ሰይፉ ወልዴ እንደተናገሩት ኤጀንሲው የተሰጠውን የአየር ትንበያ መረጃ መሰረት በማድረግ ግብረ ኃይል በማቋቋም የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው። “የክልሉ ዋነኛ አደጋ የጎርፍ ተጋላጭነት በመሆኑና በተሰጠው የአየር ትንበያ መሰረት አስፈላጊው የቅድመ ዝግጀት ስራዎች እየተከናወኑ ነው'' ብለዋል። በተሰጠው የአየር ትንበያ መሰረትም ሊከሰት ለሚችለው  አደጋ ምላሽ የሚሰጥ እቅድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ህብረተሰቡ ግንዛቤ አግኝቶ ቅድመ ጥንቃቄ በማድረግ የጎርፍ አደጋውን መካላከል እንዲችልም በክልሉ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ወቅታዊ የአየር ትንበያ መረጃዎች ተደራሽ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ የግብረና፣ የጤና፣ የውሃ፣ የትምርትና በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ተካተውበት የተቋቋመው የአደጋ መከላከል ግብረ ኃይል ለችግሩ ተጋለጭ በሆኑ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ወደ ደረቃማ ቦታዎች እንዲሰፍሩ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልጠዋል። በክልሉ በ1996 በነበረው ከመደበኛ ያለፈ የዝናብ ስርጭት ከ28 ሺህ በላይ ህዝብ በጎርፍ አደጋ ተፈናቅሎ እንደነበረ ከክልሉ የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ በጋምቤላ ከተማ የክረምቱን ወራት ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላካል እየተከናወኑ ያሉ ሰራዎችን በቅረቡ መዘገባችን ይታወሳል ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም