በ27ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ የሃዋሳ ከተማና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ለሌላ ጊዜ ተራዘመ

45
አዲስ አበባ ሰኔ 8/2010 በ27ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ከነገ በስቲያ እንዲካሄድ መርሃ ግብር ወጥቶለት የነበረው የሃዋሳ ከተማና የኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ለሌላ ጊዜ መሸጋገሩን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ገለጸ። ሁለቱ ቡድኖች እሁድ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በሃዋሳ ስታዲየም እንደሚጫወቱ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም በሃዋሳ ባለው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ምክንያት ሊራዘም መቻሉን አስታውቋል። በሌላ በኩል ነገ ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት በሚደረገው ጨዋታ ወልዋሎ በስፍራው ባለው የጸጥታ ሁኔታ ዙሪያ ማረጋገጫ እንዲሰጠው ለፌዴሬሽኑ ጥያቄ ማቅረቡን የክለቡ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዳዊት አብርሃ ለኢዜአ ገልጸዋል። የፌዴሬሽኑ የሊግ ኮሚቴ ጨዋታው በተባለው ቀንና ሰአት 'ይካሄድ አይካሄድ' በሚለው ጉዳይ ላይ ከጥቂት ሰአታት በኋላ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። በሌላ በኩል በመቐለ ስታዲየም መቐለ ከተማ ከመከላከያ ነገ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ሊካሄድ የነበረው ጨዋታ ከነገ በስቲያ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ የሚካሄድ ይሆናል። ሌሎቹ ጨዋታዎቹ ቀድሞ በወጣው መርሃ ግብር መሰረት የሚካሄዱ ይሆናል። ሊጉን ጅማ አባጅፋር በ45 ነጥብ ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ ነጥብ በጎል ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ቡናና መቀሌ ከተማ ደግሞ በ43 ነጥብና በተመሳሳይ የጎል መጠን ሶስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ አዳማ ከተማ በ42 ነጥብ አምስተኛ ደረጃን ይዟል። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት የጅማ አባጅፋሩ ናይጄሪያዊው ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ16 ጎሎች ሲመራ፤ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና የኢትዮ- ኤሌክትሪኩ ጋናዊ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም