የደም ባንኮችንና የጤና ተቋማትን የሚያስተሳስር የሞባይል መተግበሪያ ቴክኖሎጂ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ተሰራ

59
ጎንደር ሰኔ 8/2010 የደም ባንኮችንና የጤና ተቋማትን እርስ በርስ በማስተሳሰር የደም አቅርቦትንና ስርጭትን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ የሞባይል መተግበሪያ ቴክኖሎጂ በአንድ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ተማሪ ተሰራ፡፡ የሞባይል መተግበሪያው እንግሊዝኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች በቀላሉ መስራት እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የአራተኛ አመት የኢንፎርሜሽን ሲስተም ተማሪ በሆነው ወጣት ተሾመ አይችሉህም የተሰራው የሞባይል መተግበሪያ በሀገሪቱ የሚገኙ የደም ባንኮች ከለጋሾች የሚያሰባስቡትን ደም ለጤና ተቋማት በቀላሉ ለማሰራጨት የሚያግዝ ነው፡፡ የሞባይል መተግበሪያው የደም ባንኮች በእጃቸው የሚገኘውን የደም አቅርቦት መጠንና አይነት ለጤና ተቋማት በየእለቱ ማሳወቅ የሚያስችላቸው ሲሆን የደም አቅርቦት የሚገኝባቸውንም የደም ባንኮች መጠቆም የሚችል ነው፡፡ መተግበሪያው ለቋሚ ደም ለጋሾች የደም መለገሻ ቦታዎችን የሚጠቁም ሲሆን ደም የሚለገሱበትን ቀን፣ ሰአትና ቦታ ጭምር የሚጠቁምና የሚያስታውስ እንደሆነም ወጣት ተሾመ ተናግሯል፡፡ የደም ባንኮች ለደንበኞቻቸውና ለሕብረተሰቡ ጭምር ደም እንዲለግሱ ቅስቀሳና የግንዛቤ ትምህርት በየእለቱ መስጠት እንዲችሉም የሞባይል መተግበሪያው እገዛው የላቀ መሆኑ ገልጿል፡፡ ወጣት ተሾመ እንደተናገረው የሞባይል መተግበሪያውን ለመስራት ያነሳሳው ደም ባንኮች ከተለምዷዊ አሰራር ወጥተው የደም አሰባሰብና ስርጭትን ዘመኑ ባፈራው ቴክኖሎጂ ታግዘው እንዲሰሩ ለማስቻል ነው፡፡ የሞባይል መተግበሪያው በሀገሪቱ በሚገኙ ሁሉም አካባቢዎች በሞባይል ኔት ወርክ አማካኝነት መስራት የሚችል ሲሆን እንግሊዝኛን ጨምሮ በአማርኛ፣ በትግርኛና በኦሮሚኛ ቋንቋዎች በቀላሉ እንደሚሰራ ተመልክቷል፡፡ የሞባይል መተግበሪያውን የጎንደር ዩንቨርሲቲ ባለፈው ሳምንት ባዘጋጀው የቴክኖሎጂ የፈጠራ አውደ ራዕይ ላይ ለእይታ ማቅረቡን የተናገረው ወጣት ተሾመ በዩኒቨርሲቲው አማካኝነት ወደ ሙከራ ትግበራ ለማስገባት እቅድ እንዳለው ተናግሯል፡፡ የጎንደር ደም ባንክ ተወካይ አቶ ሄኖክ ወንድም በበኩላቸው “የሞባይል መተግበሪያው የደም ባንኮች በደም አቅርቦትና ስርጭት ላይ የሚታይባቸውን ክፍተት ለመሙላት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የፈጠራ ስራውን እናደንቃለን'' ብለዋል፡፡ የጎንደር ዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መስፍን በዘንድሮ አመት ለ22 የቴክኖሎጂ የፈጠራ ስራዎች ዩኒቨርሲቲው ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የበጀት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባላፈው ሳምንት ባዘጋጀው የፈጠራ ቴክኖሎጂ አውደ ራእይ የሞባይል መተግበሪያውን ጨምሮ ከ20 በላይ የፈጠራ ስራዎች ለእይታ መቅረባቸውን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ ባለፉት አመታት በዩኒቨርሲቲው መምህራንና ተማሪዎች የምርምር ስራ እውን ከሆኑ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች መካከል 11 ያህሉ ከኢትዮጵያ የአእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት የባለቤትነት መብት ማግኘት እንደቻሉም ለማወቅ ተችሏል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም