አርሶ አደሩ ምርቱን ለኢንዱስትሪ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት መስራት ይገባል.....አቶ ርስቱ ይርዳው

58
ሀዋሳ (ኢዜአ) መስከረም 19 ቀን 2012---አርሶ አደሩ ምርቱን ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ በማቅረብ የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት መስራት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አሳሰቡ። ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን ዛሬ ጎብኝተዋል። የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በጉብኝቱ ላይ እንዳሉት የይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርና ምርትን በማቀነባበርና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነቱን ያሳድጋል። በመሆኑም አርሶ አደሩ ምርቱን ለኢንዱስትሪ ፓርኩ በማቅረብ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራር አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። ፓርኩ ያመረተውን ምርት ወደ ውጭ በመላክ ለአገር የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት በኩል ትልቅ ተስፋ የተጣለበት መሆኑንም ነው አቶ ርስቱ ያስረዱት። የፓርኩ የግንባታ ሂደት በጥሩ ደረጃ እየተከናወነ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግ ነው ያመለከቱት። የፓርኩ የመሰረተ ልማት ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አቶ ርስቱ ጠቁመው የፓርኩ መገንባት  የአካባቢውን አርሶ አደሮች የተሻለ ተጠቀሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። የፓርኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው "የጉብኝቱ ዋና ዓላማ የፕሮጀክቱ አፈፃፀም ያለበትን ደረጃ መገምገምና ያጋጠሙ ችግሮችን ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር መፍትሔ ማፈላለግ ነው" ብለዋል። የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ የሙከራ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሲደረግ በታዳጊ ሀገሮች ኢንዱስትሪውን ለማስፋፋት ኢትዮጵያና ሴኔጋል ከአፍሪካ መመረጣቸውን አስታውሰዋል። "አሁን የተጀመረው ፓይለት ፕሮጀክት ስኬታማ ሲሆን ሌሎች 17 ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል" ብለዋል አቶ መለስ። ፕሮጀክቱን የዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እየተከታተለው መሆኑን ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ካሉት 4 ፕሮጀክቶች መካከል ይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ አንዱ መሆኑንና የግንባታ አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በየደረጃው ያለው የመንግስት አካልና አመራሩ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል። በፕሮጀክቱ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው ወጣቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ እና ባለሀብቶች ጭምር ከዘርፉ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም አቶ መለሰ አስረድተዋል። በጉብኝቱ አቮካዶ በማቀነባበር ላይ የሚገኘውን ፋብሪካና የፓርኩ የግንባታ ሂደት ያለበት ደረጃ ተጎብኝቷል። ፓርኩ የእንስሳት ተዋፅኦ፣ ቡና፣ አቮካዶና ማርን በማቀነባበር ወደ ውጭ ለመላክ ታስቦ እየተገነባ ያለ መሆኑን በጉብኝቱ ላይ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም