በጋምቤላ ኤች.አይ.ቪን ለመከላከል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ማስቀረት እንደሚገባ ተጠቆመ

105
ጋምቤላ ሚያዝያ 28/2010 በጋምቤላ ክልል የኤች.አይ.ቪን ስርጭት ለመግታት ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባ የክልሉ ሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ገለጹ። የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል እየተካሄዱ ባሉ ሥራዎች ላይ የአመራር አካላት፣ የሃገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት አባቶችን የአጋርነት ሚና የሚያጠናክር የምክክር መድርክ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በሰጡት አስተያየት "በክልሉ እየተስፋፋ ያለውን የኤች አይ ቪ/ኤድስ ስርጭት ለመግታት ለበሽታው የሚያጋልጡ ነባርና መጤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ አተኩሮ መስራት ይገባል" ብለዋል። በመድረኩ ከታደሙት የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ ኃይለማሪያም ተክለማሪያም እንዳሉት፣ በክልሉ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት በሚደረጉ ጥረቶች እንደ ሀገር ሽማግሌ ብዙ መስራት ይጠበቃል። በተለይ ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶችን ማዕከል ባደረገ መልኩ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት። አቶ ኃይለማርያም እንዳሉት፣ በክልሉ ለኤች.አይ.ቪ/ኤድስ አጋላጭ የሆኑ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተለይ ለቫይርሱ አጋላጭ የሆኑ በጋብቻ ላይ ጋብቻ፣ የውርስ ጋብቻና ሌሎችም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት መስራት ይገባል። "በክልሉ የበሽታውን ስርጭት ለመቀነስና ለመከላከል የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት እስከታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል በመውረድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሊሰራ ይገባል" ያሉት ድግሞ ሼክ ከድር አብዱልቃድር ናቸው፡፡ በተለይ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች ተቋማትን ማዕከል በማድረግ የሃይማኖት ተቋማት ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ፈጥረው በጋራ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ሼክ ከድር እንዳሉት፣ በክልሉ በተለይ አቅምን ያላገናዘብ ጥሎሽ ወጣቶችን ለጋብቻ የሚያነሳሳ ባለመሆኑ ለኤች.አይ.ቪ ስርጭት መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ነው። አቅምን ያላገናዘበ ጥሎሽ እንዲከፈል የሚደረግበትን አስራርና ሌሎች ጎጂ ልማዶችን ለማስቀረት የሃይማኖት ተቋማትና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። ሌላው የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ቱት ሉዋል በበኩላቸው በክልሉ የሚስተዋሉ መጤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በተለይም ሴተኛ አዳሪነት ለቫይረሱ መስፋፋት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ በመሆኑ በተለየ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ እንዳሉት፣ በክልሉ እየተስፋፋ ያለውን ኤች.አይ.ቪ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጽህፈት ቤቱ በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የተጀመሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በማጠናከር ለበሽታው አጋልጭ የሆነ ነባርና መጤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ በክልሉ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም አቶ ካን ጠይቀዋል፡፡ እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ ከእዚህ ቀደም ይህን መሰል የምክክር መድረክ አለመጠናከሩ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዳይወጡ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል። በቀጣይ በሽታውን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም