በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምቱን አግኝተዋል

117
አዲስ አበባ  ኢዜአ መስከረም 19 / 2012 በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በ5 ሺህ ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸዋል። በኳታር ርዕሰ መዲና ዶሃ እየተካሄደ የሚገኘው 17ኛው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል። በሻምፒዮናው የአራተኛ ቀን ውሎ ከሚካሄዱ ውድድሮች መካከል ከምሽቱ 3 ሰአት ከ20 ደቂቃ የሚካሄደው  የ5 ሺህ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ የሚገኝበት ሲሆን ኢትዮጵያ በአትሌት ሙክታር እድሪስ፣ አትሌት ሰለሞን ባረጋና አትሌት ጥላሁን ሃይሌ ትወከላለች። እ.አ.አ በ2017 በለንደን በተካሄደው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በ5 ሺህ ሜትር እንግሊዛዊውን አትሌት ሞሐመድ ፋራህ (ሞፋርህ) በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ሙክታር እድሪስ በአሁኑ ሰአት ያለው ወቅታዊ ብቃት ጥሩ የሚባል አይደለም። አትሌት ሙክታር በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በስዊዘርላንድ ሉዛን የዳይመንድ ሊግ ባካሄደው ብቸኛው የ5 ሺህ ሜትር ውድድር 18ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በሰኔ ወር 2019  በሀንጋሪ በተካሄደ የአትሌቲክስ ውድድር በ3 ሺህ ሜትር  ውድድር ሁለተኛ የወጣበት በዓመቱ ያስመዘገበው ጥሩ የሚባል ውጤት ነው። በአውሮፓውያን አቆጣጠር 2019 በ5 ሺህ ሜትር የዓመቱን ፈጣን ሰአት ያስመዘገበው አትሌት ጥላሁን ኃይሌ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ካገኙት አትሌቶች መካከል ይገኝበታል። በጣልያን ርዕሰ መዲና ሮም በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር በርቀቱ 12 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ98 ማይክሮ ሴኮንድ  የዓመቱን ፈጣን ሰአት ማስመዘገብ ችሏል። በ2019 ባካሄዳቸው አራት ውድድሮች በሁለቱ ሲያሸንፍ በቀሪዎቹ ሶስተኛና አራተኛ በመውጣት ጥሩ የሚባል ውጤት አስመዝግቧል። እ.አ.አ በ2019 በ5 ሺህ ሜትር ሁለተኛውን የዓለም ፈጣን ያስመዘገበው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ሌላኛው በውድድሩ ተጠባቂ አትሌት ነው። በጣልያን ርዕሰ መዲና ሮም በተካሄደው የ5 ሺህ ሜትር ውድድር 12 ደቂቃ ከ13 ሴኮንድ ከ4 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛውን ፈጣን ሰአት አስመዝግቧል። አትሌት ሰለሞን በ5 ሺህ ሜትር በ2019 አራት ውድድሮችን አካሂዶ አንዱንም ማሸነፍ ያልቻለ ሲሆን በሶስቱ ሁለተኛ ሲወጣ በቀሪው አምስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ሆኖም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በ5 ሺህ ሜትር ውድድሩን የአሸናፊነት ግምት ማግኘታቸውን የዓለም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የቅድመ ውድድር ዘገባ ያመላክታል። ወንድማማቾቹ የኖርዌይ አትሌቶች ጃኮብ፣ፊሊፕ እና ሄነሪክ ኢንግብሪግስተን በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሲሆን በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው የ19 ዓመቱ ጃኮብ ኢንግብሪግስተን የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዋንኛ ተፎካካሪ እንደሚሆን ይጠበቃል። በሌላ በኩል ከምሽቱ 3 ሰአት ከ 50 ላይ በሚካሄደው የ3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሴቶች ፍጻሜ አትሌት መቅደስ አበበ የምትሳተፍ ሲሆን አትሌቷ ወደ ፍጻሜው ለማለፍ በተደረገው ውድድር 9 ደቂቃ ከ27 ደቂቃ ከ61 ሴኮንድ በርቀቱ የግሏን ምርጥ ሰአት ማስመዝገብ ችላለች። ኬንያውያን አትሌቶች ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት አግኝተዋል። ዛሬ በዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው የአራተኛ ቀን ውሎ በሴቶች የከፍታ ዝላይና በወንዶች የዲስከስ ውርወራ የፍጻሜ ውድድሮች የሚካሄዱ ሲሆን ሌሎች የአትሌቲክስና የሜዳ ተግባራት የማጣሪያ ውድድሮችም ይካሄዳሉ። ትናንት በ10 ሺህ ሜትር ሴቶች በተካሄደ ውድድር አትሌት ለተሰንበት ግደይ የብር ሜዳሊያ በማስመዝገብ ለኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የመጀመሪያው ሜዳሊያ ማስገኘቷ የሚታወስ ነው። በውድድሩ በትውልድ ኢትዮጵያዊ በዜግነት ኔዘርላንዳዊ የሆነችው ሲፋን ሀሰን አሸናፊ ስትሆን ኬንያዊቷ አትሌት አግነስ ቲሮፕ ሶስተኛ ወጥታለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ስድስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። ትናንት በተካሄደ የ20 ኪሎ ሜትር ሴቶች የእርምጃ ውድድር አትሌት የኋልዬ በለጠው 16ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን በውድድሩ ቻይናውያን አትሌቶች ከአንድ እስከ ሶስት በመውጣት ውድድሩን በበላይነት አጠናቀዋል። በሌላ በኩል ትናንት የአራት አራት በመቶ (4x400) ድብልቅ (ወንድና ሴት) የዱላ ቅብብል የፍጻሜ ውድድር አሜሪካውያን አትሌቶች 3 ደቂቃ ከ9 ሴኮንድ ከ34 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብረዋል። የዓለም ክብረ ወሰኑ ተይዞ የነበረው ከትናንት በስቲያ በተካሄደው የውድድሩ ማጣሪያ በአሜሪካውያን አትሌቶች 3 ደቂቃ ከ 12 ሴኮንድ ከ42 ማይክሮ ሴኮንድ ሲሆን ከብረ ወሰኑ በአንድ ቀን ልዩነት በድጋሚ ተሰብሯል። የአራት አራት በመቶ (4x400) ድብልቅ(ወንድና ሴት) የዱላ ቅብብል በዘንድሮው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሰበረ የመጀመሪያው የዓለም ክብረ ወሰን ነው፡፡ የዓለም ክብረ ወሰኑ የሚጸድቀው የዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር የአበረታች መድሐኒት ምርምራ ውጤት እና ውድድሩ የሚያሟላቸው መስፈርቶች ማጣራት ከተደረገባቸው በኋላ ነው። ኢትዮጵያ በአንድ የብር ሜዳሊያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። አሜሪካ በ4 ወርቅና በ4 የብር በድምሩ በስምንት ሜዳሊያ የመጀመሪያውን ደረጃ ስትይዝ፤ ቻይና በሁለት ወርቅ፣ በሁለት የብርና  በሁለት የነሐስ በድምሩ በስድስት ሜዳሊያ ሁለተኛ፤ ጃማይካ በሁለት ወርቅና በአንድ የብር ሜዳሊያ በድምሩ በሶስት ሜዳሊያ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች። ኬንያ በአንድ የወርቅና በአንድ ነሐስ ሜዳሊያ በድመሩ ሁለት ሜዳሊያ በማግኘት አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። እስካሁን በሻምፒዮናው ከሚሳተፉ አገራት አስሩ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ገብተዋል። 17ኛው የዓለም የአትሌቲክስ ሻምፒዮና እስከ መስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም ይቆያል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም